በዩኤስ ኤድ ድጋፍ መቋረጥ ምክንያት 8 አገራት የኤችአይቪ መድኃኒት ዕጥረት እንደሚያጋጥማቸዉ ተገለጸ፡፡

የኤችአይቪ መድኃኒት ዕጥረት ያጋጥማቸዋል ሲል የዓለም ጤና ድርጅት ከጠቀሳቸዉ አገራት መካከል 6ቱ በአፍሪካ ይገኛሉ፡፡

ድርጅቱ በኤችአይቪ ፕሮግራሞች ላይ የሚፈጠር መስተጓጎል ሂደቱን 20 ዓመት ወደ ኋላ የሚመልሰዉ ነዉ ብሏል፡፡

የትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካ የውጭ ዕርዳታን ለማቆም መወሰኑ በስምንት አገራት የኤችአይቪ ሕክምና አቅርቦትን በእጅጉ አስተጓጉሏል ያለዉ ድርጅቱ፤ አገራቱ በመጪዎቹ ጥቂት ወራት የህይወት አድን መድኃኒቶች ዕጥረት ይከሰትባቸዋል ነዉ ያለዉ፡፡

በኤችአይቪ ፕሮግራሞች ላይ የሚፈጠር መስተጓጎል የለዉጥ ሂደቱን 20 ዓመት ወደኋላ የሚመልስ ነዉ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ቴዎድሮስ አድሃኖም ፤ ይህም ከ10 ሚሊየን በላይ አዳዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች እና 3 ሚሊየን ሞቶችን ያስከትላል ብለዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ፤ አሜሪካ ለአገሮች የምታደርገዉን ቀጥተኛ የገንዘብ ድጋፍ የምታቋርጥ ከሆነ፤ በሥርዓትና ሰብዓዊነት በተሞላበት መንገድ መሆን አለበት፤አማራጭ የገንዘብ ምንጭ እንዲያገኙ የሚያስችል ሁኔታ መኖሩንም የማረጋገጥ ኃላፊነት አለባት ብለዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት፤የአሜሪካ መንግስት ድጋፍ መቋረጡን ተከትሎ እስከ መጋቢት 4 ድረስ 1መቶ67 የጤና ተቋማት መዘጋታቸዉን አስታዉቆ፤ በፍጥነት እርምጃ መወሰድ ካልተቻለ እስከ ሰኔ ድረስ ተጨማሪ 2መቶ20 የጤና ተቋማት ለመዘጋት ይገደዳሉ ብሏል፡፡

ለድንገተኛ ጊዜ አደጋዎች የሚዉል የገንዘብ መጠን ከዚህ በፊት ከነበረበት 1.2 ቢሊየን ዶላር በ2026-27 በጀት ዓመት ወደ 8መቶ72 ሚሊየን ዶላር ለመቀነስ መገደዱንም ድርጅቱ አስታዉቋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በአሜሪካ መንግስት ድጋፍ መቋረጥ ምክንያት በመጪዎቹ ወራት የኤችአይቪ መድኃኒት ዕጥረት ያጋጥማቸዋል ብሎ የዘረዘራቸዉ አገራት ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ናይጄሪያ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ሌሴቶ፣ ማሊ፣ ሄይቲ እና ዩክሬን ናቸዉ ሲል ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡

እስከዳር ግርማ

መጋቢት 9 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *