የዓለም የቲቢ ህመም ቀን በየዓመቱ በማርች 24 ታስቦ ይዉላል፡፡

ዕለቱ በ1882 ዶክተር ሮበርት ኮች ቲቢ አምጪ የሆነዉን ማይኮባክቴሪየም ቲዩበርክሎሲስ ባክቴሪያን ያገኙበትን ግዜ የሚያስታዉስ ነዉ፡፡

ቲቢ አየርወለድ ተላላፊ ህመም ሲሆን፤ በቀዳሚነት ሳምባን የሚያጠቃ እና አንጎልን ጨምሮ ሌሎች የሰዉነት ክፍሎችም በቲቢ ሊጠቁ ይችላሉ፡፡

ምንም እንኳን አስቀድመን የምንከላከለዉ ፣ ህክምና ያለዉ እና መዳን የሚችል ህመም ቢሆንም በኢትዮጵያ በየዓመቱ 19ሺህ ሰዎች በሳምባ ህመም ምክንያት ህይወታቸዉ ያልፋል፡፡

በ2019 በአገራችን ከ2መቶ ሺህ በላይ አዳዲስ የቲቢ ህመምተኞች የተገኙ ሲሆን፤ ኤችአይቪ በደማቸዉ ዉስጥ የሌሉ ከ29ሺህ በላይ ዜጎች በቲቢ ህመም ምክንያት ህይወታቸዉ አልፏል፡፡

ታዲያ እኛም ዕለቱን አስመልክተን የቲቢ ህመም ተጋላጭነትን ለመቀነስ ይጠቅማሉ ያልናቸዉን ጉዳዮች ለማንሳት ወደናል፡፡

የመጀመሪያዉ ፤ ክትባት መዉሰድ ነዉ፡፡
ክትባቱ BCG ይባላል፡፡ በቲቢ ህመም ከሚመጡ ዉስብስብ ችግሮች ራሳችንን አስቀድመን የምንከላከልበት መንገድ ነዉ፡፡ በተለይ ደግሞ ለህጻናት የበለጠ ይመከራል፡፡

ክትባቱ የበሽታ መከላከል አቅማችንን ከፍ በማድረግ ባክቴሪያዉን ለመዋጋት እድል በመፍጠር አዲስ ለቲቢ ህመም የመጋለጥ ዕድላችንን ዝቅ ያደርገዋል፡፡

ሁለተኛዉ ደግሞ፤

በቤት ዉስጥ ሲሆኑ አየር እንዲገባ ማድረግ ይመከራል፡፡ በተለይ ደግሞ በቲቢ ህመም የተያዘ ሰዉ ሲያስል፣ ሲያስነጥስ ወይም ሲናገር ባክቴሪያዉ በአየር አማካኝነት ከሰዉ ወደ ሰዉ ይተላለፋል፡፡

ስለዚህ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ዉስጥ እራሶትን ካገኙ መስኮቶችን በመክፈት፣ በቤት ዉስጥ የአየር ማቀዝቀዣዎችን በመክፈት፣ በትራንስፖርት ዉስጥ ከሆኑ ደግሞ መስኮቶችን በመክፈት እና ከተጨናነቁ ቦታዎች ራሶትን በማራቅ አስቀድመዉ መከላከል ይችላሉ፡፡

ሶስተኛዉ ጉዳይ ፤

አመጋገብን በማስተካከል የበሽታ መከላከል አቅምን ማጎልበት ነዉ፡፡
በተለያዩ ንጥረ-ነገሮች የበለጸገ ምግብ መመገብ የበሽታ መከላከል አቅምን በማጎልበት ቲቢን ጨምሮ ተላላፊ የሆኑ ህመምችን ለመከላከል ይረዳል፡፡

ለምሳሌነትም፤ በቫይታሚን ሲ፣ ቫይታሚን ዲ/ፀሀይ፣ አሳ፣ እንቁላል/፣ እንደ ዚንክ/ለዉዝ፣ ጥራጥሬዎች/ እንዲሁም ፕሮቲን መመገብ የበሽታ የመከላከል አቅማችንን ጠንካራ ያደርገዋል፡፡
የበሽታ መከላከል አቅማቸዉ የወረደ በተለይ ደግሞ የስኳር እንዲሁም የኤችአይቪ ህመምተኞች ለቲቢ የመጋለጥ ዕድላቸዉ ከፍ ያለ ነዉ፡፡

አራተኛዉ ጉዳይ ደግሞ፤

የአተነፋፈስ ጤናችሁን መጠበቅ ነዉ፡፡

ታዲያ ይህ ማለት ስታስሉም ሆነ ስታስነጥሱ አፍን ወይም አፍንጫን በማስክ፣ ሶፍት፣ አልያም በክርን መሸፈን አለባችሁ ማለት ነዉ፡፡ ይሄም የቲቢ ህመም እንዳይስፋፋ ያደርጋል፡፡

የምትሰሩት በጤና ተቋማት ከሆነ አልያም ከቲቢ ህመምተኞች ጋር ቀጥታ ግንኙነት ካላችሁ ማስክ መጠቀም ከቲቢም ሆነ ከሌሎች አየር ወለድ ህመሞች መከላከያ መንገድ ነዉ፡፡

ቲቢን መከላከያ ተብለዉ ከተቀመጡ ጉዳዮች በአምስተኛነት የሚጠቀሰዉ ደግሞ፤

በቲቢ ህመም ከተጠቁ ሰዎች ጋር ከፍተኛ ቅርርብ እንዳይኖር ማድረግ ነዉ፡፡ ይህ ማለት ግን ህመምተኞችን ማግለል ማለት ሳይሆን ፤ ተገቢዉን የሆነ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ህመሙ ግን ተላላፊ በመሆኑ ተገቢዉን ርቀት መጠበቅ ይገባል ነዉ፡፡

በቋሚነት የሚደረጉ የጤና ምርመራዎች እንዲሁም የቲቢ ምርመራ ማድረግ ህመሙን ቀድሞ ለመለየት እና ወደ ሌሎች ከመተላለፉ በፊት አስቀድሞ ለመከላከል ያስችላል፡፡

ወደ ስድስተኛዉ የመከላከያ መንገድ ስናመራ ፤

ቅድመ ምርመራ በማድረግ ህመሙን ማከም ነዉ፡፡
የቲቢ ህመም ምልክቶች ሶስት ሳምንት እና ከዛ በላይ የቆየ ሳል፣ ያልታቀደበት የሰዉነት ክብደት መቀነስ፣ ማታ ላይ ላብ፣ ትኩሳት የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡

እነዚህን ምልክቶች የምታዩ ከሆነ በፍጥነት የህክምና ዕርዳታ ማግኘት ይኖርባችኋል፡፡
ቲቢ ሁለት ዓይነት ሲሆን፤ አክቲቭ እና ላተንት ይባላል፡፡

ላተንት ማለት ባክቴሪያዉ ሰዉነታችን ዉስጥ ያለ ለጊዜዉ ዝም ያለ ኢንፌክሽን ሲሆን፤ ካልታከመ ግን ወደ ህመምነት ይቀየራል፡፡
ቅድመ ልየታዎች እና ምርመራ ማካሄድ እንዲሁም በሃኪም የታዘዙ መድኃኒቶችን ጨርሶ መዉሰድ እና ህክምናዉን ማድረግ ህመሙን መከላከያ መንገድ ነዉ፡፡

የሳምባ ጤናን በቋሚ የአካል ብቃት መጠበቅ ደግሞ ሰባተኛዉ መከላከያ መንገድ ነዉ፡፡

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የሳምባ ጤናን እንዲሁም አጠቃላይ የበሽታ መከላከል አቅማችንን ያጠናክራል፡፡

እንደ የእግር እርምጃ፣ ዮጋ፣ የአተነፋፈስ ስፖርት እንዲሁም ዋና መዋኘት ሳምባችንን ለማጠናከር እንዲሁም የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሺኖችንም ለመከላከል ይረዳል፡፡
ሌላዉ ደግሞ ማጬስን ማቆም እንዲሁም ከሚያጬሱ ሰዎች መራቅ ያስፈልጋል፡፡

ስምንተኛዉ እና የመጨረሻዉ የመከላከያ መንገድ ደግሞ፤

ከተበከሉ እና ከተጨናነቁ ቦታዎች ራስን ማራቅም ይመከራል፡፡
በጣም በተጨናነቁ ቦታዎች፣ በቂ የአየር ማቀዝቀዣዎች በሌሉባቸዉ ቦታዎች ለምሳሌነትም በእስር ቤቶች እና በተፈናቃይ ካምፖች ዉስጥ የሚኖሩ ሰዎች በከፍተኛ ደረጃ ለቲቢ ተጋላጭ ናቸዉ፡፡

በእንደዚህ ዓይነት ቦታዎች ላይ መኖር አስገዳጅ ከሆነ ደግሞ የአፍ እና የአፍንጫ ጭምብሎችን ማድረግ፣ ርቀታችንን መጠበቅ፣ እንዲሁም ንጽህናን መጠበቅ ይመከራል፡፡

እስከዳር ግርማ

መጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *