በመሰረተ ልማት ግንባታዎች ምክንያት የትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ቦታ መቀየራቸዉን ተከትሎ አካል ጉዳተኞች መቸገራቸዉ ተገለጸ፡፡

በተለያዩ ቦታዎች የሚሰሩ መሰረተ ልማቶች አካል ጉዳተኞችን ያማከሉ አይደሉም ተብሏል፡፡

ከኢትዮ ኤፍኤም ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የአካል ጉዳተኛና የአረጋዉያን ስራ ክፍል ዳይሬክተር ወ/ሮ ሜቲ አቶምሳ፤ ቅሬታዉ በተደጋጋሚ ወደ ተቋማቸዉ የሚመጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመዲናዋ በተሰሩ የልማት ስራዎች የትራንስፖርት መያዣ ቦታዎች መቀየራቸዉን ተከትሎ ፤ ብዙ አካል ጉዳተኞች ለችግር መጋለጣቸዉን የሚያነሱት ዳይሬክተሯ ፤ ተቋማቸዉ በተደጋጋሚ ይህን ቅሬታ እያስተናገደ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ዳይሬክተሯ እንደሚሉት በአብዛኛዉ ዊልቼር ተጠቃሚዎች የሚጠቀሙት የትራንስፖርት አገልግሎት ባስ ነዉ፡፡

አውቶቡሶቹ  አካል ጉዳተኞችን ባማከለ መልኩ የተሰሩ ቢሆኑም አካል ጉዳተኞቹ አገልግሎት የሚያገኙት ግን በአሽከርካሪው በጎ ፈቃድ እንጂ እንደ መብት ተቆጥሮላቸዉ አይደለም ይላሉ፡፡

ለአካል ጉዳተኞች አገልግሎት ለመስጠት ፍቃደኛ ያልሆኑ አሽከርካሪዎችም ተጠያቂ ባለመሆናቸው ችግሩ እንዲሰፋ ምክንያት እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

በጤና ተቋማት እና በሌሎች ማዕከላት ለአገልግሎት የሚሄዱ አካል ጉዳተኞች በእጅጉ እየተቸገሩ ነዉ የሚሉት ዳይሬክተሯ፤በተለይ አካል ጉዳተኛ ነፍሰጡር እናቶች ጤና ተቋማት ምቹ ባለመሆናቸዉ ብዙ መጉላላት እንደሚደርስባቸዉ አንስተዋል፡፡

ይህንን ሁሉ ችግር መቅረፍ ይችላል የተባለ የአካል ጉዳተኞች መብት አዋጅ ይወጣል ከተባለ ረዥም ጊዜ መዉሰዱን የሚያነሱት ዳይሬክተሯ፤ ህጉ መዉጣቱ አስፈላጊ ቢሆንም፤ ህግ መኖሩ ብቻ ግን በቂ አይደለም መተግበር መቻል አለበት ብለዋል፡፡

በተጓተተ የመጽደቅ ሂደት ላይ የሚገኘው የአካል ጉዳተኞች ረቂቅ ሕግ ጸድቆ በአፋጣኝ ወደ ሥራ የሚገባበትን ሁኔታ አጽንዖት ሊሰጠው እንደሚገባም ኢሰመኮ ገልጿል፡፡

ሊዲያ ደሳለኝ

መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *