ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ 3.6 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት አዲስ ዘመናዊ አውሮፕላን በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በዛሬው ዕለት መረከበን አስታዉቋል።
“ሴስና ካራቫን ኤክስ” የተሰኘችው ይህች አውሮፕላን 14 መንገደኞችን የመያዝ አቅም ያላት ሲሆን፣ ባልተደራጁ የአውሮፕላን ማረፊያዎች ጭምር ማረፍ እንደምትችል ተገልጿል።
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እህት ኩባንያ የሆነው ትራንስ ኔሽንስ ኤር ዌይስ ሥራ አስኪያጅ አቶ አሚር አብዱልወሃብ እንደገለጹት፣ አውሮፕላኗ በማዕድንና በእርሻ ዘርፍ የሚደረጉ ሥራዎችን ለማሳለጥ እንዲሁም ለጎብኚዎችና ለአገልግሎት ፈላጊዎች የቻርተር አገልግሎት ለመስጠት ትውላለች።
ይህ አውሮፕላን ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ከሚገኘው ቴክስትሮን አቪዬሽን (Textron Aviation) ኩባንያ የገዛው ሲሆን ትራንስ ኔሽን ኤርዌይስ በአገር ውስጥና በአፍሪካ አህጉር የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት እንደሚዉል ተጠቁሟል።
አዲሱ አውሮፕላን በተለይ መሰረተ ልማት ባልተሟላባቸው አካባቢዎች ጭምር አገልግሎት መስጠት የሚችል በመሆኑ ለሀገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም
