በኢ-መደበኛ ንግድ ላይ የተሰማሩ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ደንብ ተዘጋጀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይፋ ያደረገው አዲስ ደንብ በኢ-መደበኛ ንግድ ላይ የተሰማሩ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ተብሏል፡፡

” የጎዳና ላይ ንግድን አናበረታታም ነገር ግን በዚህ ኢ-መደበኛ ንግድ ላይ የተሰማሩ በርካታ ዜጎች በመኖራቸው ወደ ህጋዊ መስመር እንዲገቡ የማድረግ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው ” ሲል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ገልጿል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የህግ አገልግሎት ሃላፊ አቶ መለሰ ተገኑ ለኢትዮ ኤፍኤም እንደተናገሩት በዘርፉ በርካታ ሰዎች የተሰማሩበትንና የራሱ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያለውን የጎዳና ላይ ንግድን ስርዓት ባለው መልኩ ለማስኬድ፣ ብሎም በስራው ላይ የተሰማሩ ዜጎችን ወደ ህጋዊ መስመር ለማስገባት ደንብ ወደ ስራ መግባቱን አስረድተዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ መደበኛ ያልሆነ የጎዳና ላይ ንግድ ስርዓት ያስይዛል በማለት ይፋ ያደረገው የደንብ ቁጥር 184/2017፣ በአምስት ክፍሎችና በ34 አንቀጾች ተዋቅሮ የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም እንደጸደቀ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮን ጨምሮ በከተማ አስተዳደሩ ስር ያሉ የተለያዩ ባለድርሻ የመንግስት ኣካላት በጋራ በመሆን ደንቡን እንደሚያስፈጽሙም አክለዋል፡፡

የደንቡን መውጣት ተከትሎ በጎዳና ንግድ ላይ የተሰማሩ ዜጎች የግብር ከፋይ መለያ ቁጥርን ጨምሮ ማሟላት ያሉባቸውን መስፈርቶች በማሟላት እውቅና ተሰቷቸው ወደ ስራ ይገባሉ ሲሉ የከተማዋ ንግድ ቢሮ የህግ አገልግሎት ሃላፊ አቶ መለሰ ተገኑ ገልጸዋል፡፡

የደንቡ መጽደቅ በኢ-መደበኛ ንግድ ላይ የተሰማሩ ዜጎችን ወደ መደበኛ ንግድ እንዲገቡ ከማድረግ በተጨማሪ ኮንትሮባድን ፣ በትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት የሚደርስ አደጋንና በህጋዊ ንግዱ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ እንደሚቀርፍም ነው ያብራሩት፡፡

በደንቡ መሰረት የጎዳና ላይ ንግዱን የሚያካሂዱ ነጋዴዎች የስራ ሰዓታቸው በ5 ፈረቃ የተከፋፈለ ሲሆን ወደፊት እየታየ ቸግሮች ካሉ የሚስተካከሉ ይሆናል ብለዋል፡፡

አዲስ አለም አበበ

መጋቢት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *