ትራምፕ “አክብሮት ይጎድላታል” ባሏት ቻይና ላይ ተጣለውን ቀረጥ ወደ 125 በመቶ አሳድገዋል።

ቻይና በበኩሏ ይህን አይነቱን “አጉራ ዘለል ተግባራት” እንደምትቃወም አስታውቃለች፡፡

ፕሬዝደንት ትራምፕ ከቻይና ጋር የገቡበት የንግድ ጦርነት ግን እየተባባሰ ቀጥሏል።

በሌላ በኩል ትራምፕ በአገራት ላይ የጣሉትን ከፍተኛ ታሪፍ ተፈጻሚነት ለ90 ቀናት ማዘግየታቸውን አስታውቀዋል፡፡

60 ገደማ በሆኑ የአሜሪካ አጋር አገራት ላይ ተጣለው ቀረጥ ተፈጻሚ መሆን በጀመረ በሰዓታት ውስጥ ትራምፕ አስገራሚ በሆነ የፖሊሲ ለውጥ የከፍተኛ ታሪፍ ተፈጻሚነትን አዘግይተዋል።

በዚህ መሰረት ከአገራቱ ጋር የሚደረገው ድርድር እንዲቀጥል እና ሁሉም አገራት የሚከፍሉት “ዝቅተኛ የሆነውን 10 በመቶ ቀረጥ” እንዲሆን ተደርጓል።

ትራምፕ ይህንን ውሳኔ ባስተላለፉ በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ “አክብሮት ይጎድላታል” ባሏት ቻይና ላይ ተጣለውን ቀረጥ ወደ 125 በመቶ አሳድገዋል።

ፕሬዝዳንቱ በቻይና ላይ ይህንን ውሳኔ ያሳለፉት ቤጂንግ ከአሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ የ84 በመቶ ቀረጥ እንደምትጥል ማስታወቋን ተከትሎ ነው።

ከሰዓታት በኋላ አዲሱ ለውጥ ይፋ ሲደረግ ግን በገበያው ላይ አዎንታዊ ለውጥ ታይቷል።

ትራምፕ፤ በ”ትሩዝ” ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ አሜሪካ ለጣለችው ቀረጥ አጸፋዊ ምላሽ ባልሰጡ አገራት ላይ ተፈጻሚነቱ ለ90 ቀናት እንዲዘገይ ማዘዛቸውን አስታውቀዋል።

በቻይና ላይ የተጣለውን ተጨማሪ ቀረጥ ግን ወዲያውኑ ተፈጻሚ መሆን እንደሚጀምር ገልጸዋል።

ትራምፕ፤ቻይና ይህንን የአጸፋ ምላሿን የማትቀለብስ ከሆነ ተጨማሪ 50 በመቶ ቀረጥ በመጣል አጠቃላይ የታክስ መጠኑን 104 በመቶ እንደሚያደርሱት ማክሰኞ ዕለት ዝተው ነበር።

ከውሳኔዋ ያላፈገፈገችው ቻይና ግን፤ አሜሪካ “የቀረጥ ወይም የንግድ ጦርነት መቆስቆስ ከቀጠለች”፤ “እስከ መጨረሻው እንደምትዋጋ” ተናግራለች።

ትራምፕ በቻይና 104 በመቶ ቀረጥ ከጣሉ ከሰዓታት በኋላ ቤጂንግ ከአሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ የተጣለውን ቀረጥ ከ34 በመቶ ወደ 84 በመቶ ከፍ እንደምታደርግ አስታውቃለች።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሊን ጂያን፤ አሜሪካ “ተንኳሽ በሆነ ሁኔታ ቻይና ላይ ቀረጥ መጣል ቀጥላለች” ብለዋል።

ቻይና ይህን አይነቱን “አጉራ ዘለል ተግባራት” እንደምትቃወም የተናገሩት ቃል አቀባዩ አሜሪካ ጉዳዩን በድርድር የመፍታት ተስፋ ካልት “የእኩልነት፣ የመከባበር እና የመደጋፍ አመለካከት” ልታሳይ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሚያዚያ 2 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *