ፕሮጀክቱ በሶስት ክልሎች በሚገኙ በ8 ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ ነዉ፡፡
ኤስ ኦ ኤስ የህጻናት መንደር የሰላም ፕሮጀክት ከአዉሮፓ ህብረት በተገኘ የ2 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ የሚተገበር ነዉ፡፡
በአፋር ፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በሚገኙ አጎራባች ወረዳዎች ላይ የሚተገበር ሲሆን፤የማህበረሰቡን ግንኙነቶች በማጠናከር በድጋሜ የሚቀሰቀሱ ግጭቶችን ለመከላከል፣ለመቀነስና ለመግታት ታቅዶ የተዘጋጀ ነው።
እስከ 2027 ድረስ የሚቆየው ይህ የሶስት አመት ፕሮጀክት፤8 አጎራባች ወረዳዎች ላይ የሚሰራ ሲሆን፤ በቀጥታ 45ሺህ6መቶ79 ወጣቶችን ፣ሴቶችን፣የሀይማኖት መሪዎችንና ማህበረሰብ የሚደግፍ ነዉ ተብሏል።
የኤስ ኦ ኤስ የህጻናት መንደሮች በኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን ብሄራዊ ዳይሬክተር አቶ ሣህለማርያም አበበ፤ፕሮጀክቱ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና የማህበረሰብ ደህንነት ጉልህ ሚና አለዉ ብለዋል፡፡
የሴቶችን ፣የወጣቶችን ፣ እንዲሁም ከማህበረሰቡ የተወጣጡ ሀገር በቀል ድርጅቶችን አቅም በማጎልበት አንድነትን ፣መተሳሰብን የሚያስቀድም ህብረተሰብን ለመገንባት የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ አስታዉቀዋል።
ኤስ ኦ ኤስ ይህን ፕሮጀክት የሚተገብረው ከሰላም ሚኒስቴር ፣ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከግብርና ሚኒስቴር እንዲሁም ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እንደሆነ አስታዉቋል፡፡
ሊዲያ ደሳለኝ
ሚያዚያ 2 ቀን 2017 ዓ.ም
