በዞኑ ደጋማ አካባቢዎች የመሬት መንሸራተት እና የመሬት ናዳ አደጋ ስጋት ያለባቸዉ መሆኑ ተነግሯል።
በደብብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን የመሬት መንሸራተት ስጋት ላይ ያሉ ቀበሌዎች እየተለዩ መሆኑን ሰምተናል።
የዞኑ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ማርቆስ መለሰ ለኢትዩ ኤፍኤም እንደገለፁት በዞኑ አሁንም በርካታ አካባቢዎች ስጋት ዉስጥ ናቸዉ ብለዋል።
በባለፈዉ አመት በዞኑ አጋጥሞ የነበረዉ የመሬት መንሸራተት ያስታወሱት ሀላፊዉ በመጪዉ ክረምት የቅድመ አደጋ መከላከል ስራ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በተደረገ የአደጋ ስጋት አመራር ጥናት መሰረትም በጎፋ ዞን የሚገኙ አጠቃላይ ወረዳዎች ላይ ቀበሌዎችን በአረንጓዴ እና በቢጫ መለያ በመስጠት እየተለዩ እንደሚገኝ ሀላፊዉ ለኢትዩ ኤፌም አስታዉቀዋል።
የዞኑ አካባቢዎችን ስነ ምህዳር መሰረት ያደረገ ጥንቃቄ እንዲደረግ ከኢጋድ እና ከብሄራዊ ሜትሮዎሎጂ እየተሰጡ ያሉ መረጃዎችን መነሻ እየተደረገ ነዉ ተብሏል።
የጎፋ ዞን የአደጋ ስጋት ፅህፈት ቤት ሀላፊዉ አቶ ማርቆስ መለሰ ብዙ ነዋሪዎች የባለፈዉ አመት ተመሳሳይ አደጋ እንዳይገጥማቸዉ ያልተቋረጠ ድጋፍ ያስፈልገናል ብለዋል።
ሀምሌ 15 ቀን 2016 አ.ም በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ አጋጥሞ በነበረዉ አደጋ 246 ሰዎች ህይወት እንዲያልፍ አድርጓል።
ሆኖም አሁንም ስጋት ላይ ያሉ ቀበሌ ነዋሪዎችን ከአካባቢዎቹ ቀድሞ ለማዉጣት ያሉ እንቅስቃሴዎች ድጋፍ የሚያስፈልገን ነዉ ሲሉ ሀላፊዉ ለ ጣቢያችን ገልፀዋል።
አቶ ማርቆስ በህይወት የተረፉትን ነዋሪዎች የመልሶ ማቋቋም ስራን በተመለከተ የቤቶች ግንባታ እየተከናወነ ነዉ ብለዋል።
ከወራት በፊት የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ተጎጂዎችን በመለየት 110 ቤቶችን በመገንባት ማስረከብ መቻሉን እንዲሁም 420 ቤቶችም እየተገነቡ ነዉ ተብሏል ።
ቁምነገር አየለ
ሚያዚያ 06 ቀን 2017 ዓ.ም
