ትናንት ጠዋት ከሆስፒታሉ ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ እንደተሰጠ እንዲሁም ጥቃትም መድረሱን የአለም ጤና ድርጅት ገልጿል።
ድርጅቱ ከሆስፒታሉ ዳይሬክተር ደርሶኛል ባለው ሪፖርት መሰረት፤ በተፈጠረው ግርግር የህክምና እርዳታ ማግኘት ባለመቻሉ አንድ ልጅ ህይወቱ አልፏል።
በሆስፒታሉ የድንገተኛ ክፍል፣ የላቦራቶሪ እንዲሁም የድንገተኛ ጊዜ የጨረር ማሽኖች እና መድኃኒት ክፍሉ ወድመዋል።
50 ህመምተኞችን ወደ ሌሎች ሆስፒታሎች ለማዘዋወር መገደዱ የተገለፀ ሲሆን፤ 40 የሚሆኑ ፅኑ ህሙማን ግን እዛው እንዲቆዩ ተደርጓል ነው የተባለው።
በዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ መሰረት ሆስፒታሎች ከአደጋ የመጠበቅ መብት አላቸው ያለው የአለም ጤና ድርጅት፤ በጤና ተቋማት ላይ የሚደርስ ጥቃት ሊቆም ይገባል ብሏል።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድኃኖም፤ ታካሚዎች፣ የጤና ባለሙያዎች እንዲሁም ሆስፒታሎች የግድ ሊጠበቁ ይገባል ያሉ ሲሆን፤ የዕርዳታ ገደቡ መነሳት አለበት የተኩስ አቁም ስምምነት ይደረግ ሲሉ አሳስበዋል።
እስከዳር ግርማ
ሚያዚያ 06 ቀን 2017 ዓ.ም
