በአዲስ አበባ ሊካሄድ የታቀደው የፓኪስታን-አፍሪካ የንግድ ልማት ጉባኤ መራዘሙ ተገለፀ፡፡

ከ100 በላይ የፓኪስታን ኩባንያዎች ይሳተፉበታል የተባለው 5ኛው የፓኪስታን-አፍሪካ የንግድ ልማት ጉባኤ እና የፓኪስታን ምርቶች አውደ ርዕይ ሃገሪቱ ከጎረቤቷ ህንድ ጋር በገባችበት ውዝግብ ምክንያት መራዘሙን ጣቢያችን ሰምቷል፡፡

በኢትዮጵያ የፓኪስታን ኤምባሲ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሳወቀው ከሰሞኑ በኢዝላማባድና ኒውደልሂ መካከል ተነስቶ በነበረው ጦርነት ምክንያት የንግድ ልማት ጉባኤውና አውደ ርዕዩ በተያዘለት ጊዜ ሊከናወን አልቻለም፡፡

በኤምባሲው የንግድ ልማት መኮንን የሆኑት መኪዩ ያዕቆብ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ ከግንቦት 7 እስከ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ በሚሊኒየም አዳራሽ እንዲካሄድ መርሐ ግብር ተይዞለት የነበረው 5ኛው የፓኪስታን-አፍሪካ የንግድ ልማት ጉባኤ እና የፓኪስታን ምርቶች አውደ ርዕይ፣ በፓኪስታንና ህንድ ውዝግብ ምክንያት ወደ ሌላ ቀን ተላለፏል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ፓኪስታንና ህንድ የተኩሰ አቁም ያደረጉ ቢሆንም መርሐ ግብሩ ከተያዘ በኋላ በሃገራቱ መካከል በጣት ለሚቆጠሩ ቀናት ተፈጠሮ የነበረው ጦርነት ሁነቱ እንዲራዘም ማድረጉን የነገሩን የኤምባሲው የንግድ ልማት መኮንን፣ ለጊዜው ቀን እንዳልተቆረጠና የተስተጓጎለውን ጉባኤ ለማስተካከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጉባኤው ይከናወንበታል የተባለውን ሚሊኒየም አዳራሽን ጨምሮ ከሌሎችም አካላት ጋር ለማስተካከል እየሰሩ መሆኑንም አክለዋል፡፡

አዲስአለም አበበ

ግንቦት 7 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *