የኢነርጂ ስርቆት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችና ቡድኖች እየተበራከቱ መጥተዋል ሲል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ

በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የተገዙ የኤሌክትሪክ ኃይል ማሰራጫ መስመሮች ላይ ጉዳት፣ ውድመትና ስርቆት የሚፈፅሙ ብሎም የኢነርጂ ስርቆት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችና ቡድኖች እየተበራከቱ መምጣታቸዉን ተቋሙ አስታዉቋል፡፡

የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለአንድ ሀገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ዋነኛ ምሰሶ ነዉ ያለዉ ተቋሙ፤የቴሌኮሚኒኬሽንና የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን ለመጠበቅ የወጣ አዋጅ መኖሩንም ገልጿል፡፡

በአዋጁ መሰረት የኤሌክትሪክ ኃይል የሰረቀ፣ በሕገ ወጥ መንገድ ከሌላ መስመር ጋር ያገናኘ፣ መሰመሩን ያሰናከለ፤ ከተሰረቀ መስመር በህገ ወጥ መንገድ መስመሩን ከሌላ መስመር ጋር ያገናኘ፤ እያወቀ ከዚህ መስመር የኤሌክትሪክ ኃይል ለፍጆታ ያዋለ እስከ 5 አመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ወይም እስከ 25 ሺህ ብር እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡

ይሁንና አዋጁን ወደጎን በመተው ከብዙኃን ጥቅም ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም በማስቀደም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የተገዙ የኤሌክትሪክ ኃይል ማሰራጫ መስመሮች ላይ ጉዳት፣ ውድመትና ስርቆት የሚፈፅሙ ግለሰቦችና ቡድኖች እየተበራከቱ መምጣታቸዉን የተቋሙ መረጃ ያሳያል፡፡

ባለፉት 9 ወራት ከኤሌክትሪክ መሰረተ ልማትና ከኃይል ስርቆት ጋር በተገናኘ ከ199 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን ጉዳቱን ባደረሱ አካላት ላይ 208 የክስ መዝገቦች መከፈታቸውንም አገልግሎቱ ተናግሯል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ 27 መዝገቦች ላይ ውሳኔ ተሰጥቷል የተባለ ሲሆን በዚህም ከ2 ወር እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከ25 ሺህ እስከ 50 ሺህ ብር የሚደረስ የገንዘብ ቅጣት ተላልፎባቸዋል ተብሏል፡፡

ልኡል ወልዴ

ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *