ኢራቅ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ የሚሠሩ እና እጅግ አስፈላጊ ሥራ የሌላቸው ሠራተኞች እና ቤተሰቦቻቸው በከፍተኛ የደህንነት ስጋት ምክንያት ሊወጡ እንደሆነ የአሜሪካ መንግሥት ምንጭ ተናግሯል።
የደህንነት ስጋት የተባለውን ጉዳይ ምንነት በአሜሪካ ባለስልጣናት በኩል በግልጽ ባይነገርም ትናንት ረቡዕ እስራኤል በኢራን ውስጥ ‘ጥቃት’ ልታካሂድ እንደሆነ ለአሜሪካ መነገሩን በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ሲቢኤስ ባለስልጣናትን ጥቅሶ ዘግቧል።
ይህም አሜሪካ ከቀጠናው የኤምባሲ ሠራተኞችን የምታስወጣበት አንደኛው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ባለስልጣኑ ገልጿል።
ይህ የሚሆነው በእስራኤል ‘ጥቃት’ ምክንያት ኢራን በኢራቅ በሚገኙ የአሜሪካ ይዞታዎች ላይ የአጸፋ እርምጃ ትወስዳለች በሚል ስጋት ነው።
ይህ ዜና የተሰማው አሜሪካ ከኢራን ጋር በቴህራን የኒውክለር ፕሮግራም ዙሪያ የሚያደርጉት ንግግር መቋረጡ በተሰማ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ነው ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም
