ባለሙያዎቻችን ለህይወታቸው የሚያሰጉ ዛቻዎችን እየተጋፈጡ ጭምር ነው የሚሰሩት ሲል የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን በምግብ ጥራትና ደህንነት ላይ ክትትል የሚያደርጉ ባለሙያዎቹ ለህይወታቸው የሚያሰጉ ዛቻዎችን ጭምር እየተጋፈጡ እንደሚሰሩ ገልጿል።

ባለስልጣኑ የምግብ ጥራትና ደህንነትን ለማስጠበቅ በሚያደርገው ምርመራና ክትትል የሚያሰማራቸው ባለሙያዎች ላይ ያልተረጋገጡ ውንጀላዎች እንደሚሰነዘሩም ጠቅሷል።

የባለስልጣኑ ምግብ ኢንስፔክሽንና የህግ ማስፈጸም መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙላቱ ተስፋዬ ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር በነበራቸው ቆይታ ባለሙያዎቻችን የትኛውም ድርጅት ውስጥ ገብተው የክትትል ስራ እንዲሰሩ፣ የህብረተሰቡን ጤና የሚጎዱ ተግባራትን እንዲለዩ የተሰጣቸው ስልጣን አለ ብለዋል።

ሆኖም ግን ተቆጣጣሪ አካላት ያልተረጋገጡ ውንጀላዎች ሲሰነዘርባቸው ይታያል ያሉት አቶ ሙላቱ፣ ለህብረተሰቡ የጥንቃቄ መልዕክቶችን ስናስተላልፍ እንኳን “ገንዘብ አንሰጥ ስለተባላቹ ነው ?” የሚሉና ሌሎችም አሉታዊ አስተያየቶች እንደሚንፀባረቁ ተናግረዋል።

ይህ ማለት ግን በተቆጣጣሪዎች ላይ ችግር የለም ማለት እንዳልሆነም ነው የገለፁት።
ባለስልጣኑ ተቆጣጣሪ አካል በመሆኑና የስራው ሂደትም ለሙስና ተጋላጭ ስለሆነ ሙስናን ለመቆጣጠር የሚያስችል አሰራር አለን ብለዋል።

በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የእንሰሳት ተዋፅዖና አልሚ ምግቦች ኢንስፔክሽን ዴስክ ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን በበኩላቸው ለጣቢያችን በሰጡት ቃል፣ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎቻቸው ሲቪሎች በመሆናቸው ለጥቃት ተጋላጭ እንደሆኑ ገልፀዋል።

“እኛ ሲቪል ሰራተኞች እንጂ የፀጥታ አካል አይደለንም። ቁጥጥር የምናደርግበት አካል ሊያጠቃን ቢፈልግ በቀላሉ መከላከል አንችልም” ያሉት አቶ መሐመድ፣ እንዲህ ዓይነት ችግሮችን እየተጋፈጥን ነው የምንሰራው በማለት ተናግረዋል።

አዲስአለም አበበ

ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *