ፕሬዝዳንቱ ሁለቱን አገራት ለማሸማገልም ሀሳብ አቅርበዋል፡፡
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር ስለ እስራኤል እና ኢራን ቀውስ በስልክ መነጋገራቸዉን ገልጸዋል፡፡
በሩሲያ መንግስት የሚተዳደረዉ ታስ የዜና ወኪል እንደዘገበዉ፤ ሁለቱም መሪዎች በሁኔታዉ የገባቸዉን ጥልቅ ስጋት በመግለጽ፤ፈጣን መፍትሄ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል፡፡
በስልክ ንግግራቸዉ ወቅት ፑቲን ሩሲያ ቀውሱን ለማሸማገል ፍቃደኛ መሆኗን ተናግረዋል ነዉ የተባለዉ፡፡
በተያያዘ ዜና፤ የሩስያ ባለስልጣን አሜሪካ ለእስራኤል የምትሰጠው ዕርዳታ መካከለኛው ምስራቅን ሊያናጋ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡
የሩስያ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ሪያብኮቭ፤አሜሪካ ለእስራኤል የምትሰጠው ቀጥተኛ ወታደራዊ እርዳታ የአየር ጦርነት በተቀሰቀሰበት በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ሁኔታ በእጅጉ ሊያዛባው እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ሪያብኮቭ ፤ሩሲያ አሜሪካን ለእስራኤል እንዲህ አይነት እርዳታ እንዳትሰጥ ወይም ለመደገፍ እንዳታስብም ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች ብለዋል፡፡
ሞስኮ ከእስራኤል እና ከኢራን ጋር መነጋገሯንም አስታዉቀዋል ሲል አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
እስከዳር ግርማ
ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም
