የፓርላማዉ አፈ-ጉባዔ የኢራን ሰላማዊ የኒውክሌር መርሃ ግብር በፍጥነት መካሄዱን ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ፓርላማዉ ዛሬ ጠዋት ኢራን ከተባበሩት መንግስታት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ድርጅት ጋር ያላትን ትብብር እንድታቆም ድምጽ ሰጥቷል፡፡
አሜሪካ ከእስራኤል ጋር እንዲደረግ ያቀረበችው የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ ከሆነ ከአንድ ቀን በኋላ ዉሳኔዉ መተላለፉ ተገልጿል።
የኢራን የአቶሚክ ኢነርጂ ድርጅት የኑክሌር ተቋማት ደህንነት እስኪረጋገጥ ድረስ ከአለም ዓቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር ያለውን ትብብር ያቆማል ሲሉ የፓርላማዉ አፈ-ጉባዔ ተናግረዋል፡፡
አፈ-ጉባዔዉ በተጨማሪም የኢራን ሰላማዊ የኒውክሌር መርሃ ግብር በፍጥነት ይካሄዳል ብለዋል፡፡
ትብብሩን ለማቆም የቀረበው ረቂቅ ህግ በ2መቶ22 የድጋፍ ድምጽ ያለምንም ተቃውሞ በአንድ ድምጸ ተአቅቦ ጸድቋል።
አፈ-ጉባዔዉ ፤በምንም አይነት ተስፋዎች አንታለልም ለማንኛውም ጥቃት ጠንከር ያለ ምላሽ ለመስጠት ከበፊቱ የበለጠ ዝግጁ እንሆናለን ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል፡፡
በፓርላማው ውሳኔ መሠረት የኤጀንሲው ወኪሎች የሀገሪቱ የኒውክሌር ተቋማት ደህንነት እና ሰላማዊ የኒውክሌር እንቅስቃሴ እስካልተረጋገጠ ድረስ ወደ ሀገር ቤት የመግባት መብት የላቸውም።
እስራኤል በሰኔ 6 ወታደራዊ እና የኒውክሌር መስሪያ ቤቶችን ጨምሮ በተለያዩ የኢራን ጣቢያዎች ላይ የአየር ድብደባ መጀመሯ የሚታወስ ሲሆን፤ ቴህራን የኒውክሌር ቦምብ ልታመርት ነው በሚል በኢራን ላይ የከፈተችዉን ክስ አጠናክራዋለች፡፡
ኢራን አጸፋዊ የሚሳኤል እና ሰው አልባ ጥቃቶችን ስትፈጽም፤አሜሪካ በበኩሏ ሶስት የኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ በቦምብ ጥቃት በማድረስ ግጭቱን በይፋ መቀላቀሏን አስታዉቃለች፡፡
የአሜሪካዉ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከ12 ቀናት የአየር ላይ ዉጊያ በኋላ በእስራኤል እና በኢራን መካከል የተጠናከረዉን ዉጥረት ለማርገብ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረጋቸውን ማስታወቃቸዉ ይታወሳል ሲል አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
እስከዳር ግርማ
ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም
