ትራምፕ በብሪክስ አባል አገራት ላይ ተጨማሪ 10 በመቶ ታሪፍ እንደሚጥሉ ዛቱ

ትራምፕ ከብሪክስ ‹‹ፀረ-አሜሪካዊ ፖሊሲዎች››ጋር የሚስማሙ ሀገራት ተጨማሪ ታሪፎች እንደሚጣልባቸዉ አስጠንቅቀዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤በትናንትናዉ ዕለት በብራዚል የመሪዎች ስብሰባዉን የጀመረዉ የብሪክስ ቡድን የሚያራምደዉ ‹‹ፀረ አሜሪካዊ ፖሊሲዎች›› ጋር የሚስማማ ማንኛውም ሀገር ተጨማሪ የ 10 በመቶ ቀረጥ ይጣልበታል ብለዋል፡፡

እንደ G7 እና G20 ያሉ ዋና የኢኮኖሚ መድረኮች በክፍፍል እየተናጡ ባለበት ሁኔታ ፤ብሪክስ በአመጽ፣ ግጭቶች እና የንግድ ጦርነቶች ውስጥ እራሱን የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ መሸሸጊያ አድርጎ እያቀረበ ነው።

እሁድ ከሰአት በኋላ በሪዮ ዲጄኔሮ በተጀመረዉ በብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ መክፈቻ ላይ ቡድኑ ባወጣው የጋራ መግለጫ፤የታሪፍ መጨመር የአለምን ንግድ ስጋት ላይ ጥሎታል ሲል በትራምፕ የታሪፍ ፖሊሲ ላይ የሚሰነዝረዉን ትችት መቀጠሉን አስታዉቋል፡፡

ከሰዓታት በኋላም ትራምፕ ከቡድኑ ጋር ለመቀላቀል የሚፈልጉ ሀገራትን እንደሚቀጡ አስጠንቅቀዋል።

የትራምፕ አስተዳደር የአጸፋ ታሪፍ ለመጣል ከሐምሌ 9 ቀነ ገደብ በፊት ከብዙ ሀገራት ጋር በደርዘን የሚቆጠሩ የንግድ ስምምነቶችን ለማጠናቀቅ ይፈልጋል።

የመጀመሪያው የብሪክስ አባል አገራት ብራዚል ፣ ሩሲያ ፣ ህንድ እና ቻይና መሪዎች በ2009 ስብሰባ አድርገዋል፡፡

ህብረቱ በኋላ ላይ ደቡብ አፍሪካን ጨምሯል፡፡ ባለፈው ዓመት ደግሞ ግብፅ ፣ ኢትዮጵያ ፣ ኢንዶኔዥያ ፣ ኢራን እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በአባልነት ተካተዋል፡፡

ሳዑዲ አረቢያ በይፋ ወደ ህብረቱ መቀላቀልን ያቆመች ሲሆን፤ ሌሎች 30 ሀገራት ግን በብሪክስ ሙሉ አባልነት ወይም አጋርነት የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል ሲል ሮይተርስ ነዉ የዘገበዉ።

እስከዳር ግርማ

ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *