የሁቲ አማጽያን በአንድ ሳምንት ውስጥ ሁለተኛውን የቀይ ባህር የጭነት መርከብ አሰጠሙ

የየመን ሁቲዎች በጉዞ ላይ የነበረ የጭነት መርከብ ላይ ጥቃት ከፈጸሙ እና መርከቡ ቀይ ባህር ውስጥ ከሰጠመ በኋላ ስድስት መርከበኞች መትረፋቸውን እና ቢያንስ ሦስት ሌሎች ሰዎች መሞታቸውን የአውሮፓ የባህር ኃይል ተልዕኮ አስታወቀ።

የላይቤሪያን ባንዲራ የሚያውለበልበው እና በግሪክ የሚንቀሳቀሰው ‘ኤተርኒቲ ሲ’ የተባለው የጭነት መርከብ 25 ሠራተኞችን ይዞ እየተጓዘ ነበር።

መርከቡ ሰኞ ዕለት ከትንሽ ጀልባዎች በተተኮሱ የሮኬት ቦምቦች ከተመታ በኋላ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን በዚህም የመንቀሳቀስ አቅሙን እንዳጣ የእንግሊዝ የባሕር ንግድ ሥራዎች ኤጀንሲ (UKMTO) ገልጿል።

ጥቃቱ ማክሰኞ ዕለትም ቀጥሎ የዋለ ሲሆን መርከበኞቹን የማዳን ሥራ የተጀመረው ሌሊት ላይ ነው።

በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች፤ ኤተርኒቲ ሲ ላይ ጥቃት የፈጸሙት ወደ እስራኤል እየተጓዘ ስለነበረ እንደሆነ አስታውቀዋል።

ቁጥራቸው ያልታወቀ ሠራተኞችንም “ደህንነቱ ወደ የተጠበቀ ቦታ” እንደወሰዱ ተናግረዋል።

በየመን የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ሁቲዎች “በሕይወት የተረፉ የቡድን አባላትን አፍነው መውሰዳቸውን” ገልጾ፤ በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ጥሪ አቅርቧል።

የፊሊፒንስ ባለስልጣናት ከቡድኑ አባላት ውስጥ 21 ያህሉ ዜጎቻቸው እንደሆኑ ተናግረዋል።

ከቀሪዎቹ መካከል አንዱ የሩስያ ዜግነት ያለው እንደሆነ እና በጥቃቱ በደረሰበት ከፍተኛ ጉዳት እግሩን እንዳጣም ተገልጿል።

ሁቲዎች በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ይህንን ዓይነቱን ጥቃት ሲፈጽሙ ይህ ሁለተኛቸው ነው።

ሐምሌ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *