በክልሉ 5 ሚሊዮን 5 መቶ 18ሺ ሰዎች ምርመራ ተደርጎላቸው 2 ሚሊዮን 80 ሺ የሚጠጉ ሰዎች ወባ እንደተገኘባቸው የአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ የወባ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዳምጤ ላንክር ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት በክልሉ ምዕራባዊ ክፍል የሚገኙ ዞኖች ከፍተኛ የወባ ስርጭት ያለባቸው ሲሆኑ 90 በመቶ የሚሆነውን የክልሉን ስርጭት ይሸፍናሉ፡፡
ከፍተኛ የሆነ የስርጭት መጠን ከተመዘገበባቸው ዞኖች መካከል ደቡብ ጎንደር 4 መቶ አራት ሺ የሚሆኑ ፣አዊ ዞን ከ3መቶ ሺ በላይ ፣ማዕከላዊ ጎንደር ዞን 2መቶ 29ሺ የሚሆኑ እንዲሁም የምዕራብ ጎጃም ዞን 1መቶ 87 ሺ የሚጠጉ ህሙማን ሪፖርት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በክልሉ በጤና ተቋማት ከሚሰጡ ህክምናዎች ውስጥ የወባ ህክምና 8 በመቶውን እንደሚሸፍን የገለፁት ሀላፊው በ2017 አ.ም 98 ሰዎች በወባ በሽታ ህይወታቸውን አተዋል ብለዋል፡፡
ዘንድሮ የተመዘገበው የወባ ህሙማን ቁጥር ከባለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር በ37 በመቶ መቀነሱን አቶ ዳምጤ ላንክር ተናግረዋል፡፡
ሐመረ ፍሬው
ሐምሌ 3 ቀን 2017 ዓ.ም
