የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ እና ስራዎች ኤጀንሲ በጋዛ የሰብአዊ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን አስጠንቅቋል።
በተለይም በህጻናት እና ሌሎች ተጋላጭ በሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ገልጿል፡፡
የጤና አጠባበቅ ስርዓቱም ሙሉ በሙሉ መውደቁን ኤጀንሲው አስታዉቋል፡፡
ኤጀንሲው ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤በጋዛ ሰርጥ የድጋፍ አቅርቦት ላይ የተጣለዉ ከባድ እገዳ እንደቀጠለ በመሆኑ ወደ 70 ሺህ የሚጠጉ ህጻናት እና ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ ለከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ተዳርገዋል።
በተጨማሪም በእነዚህ አስከፊ ሁኔታዎች ውስጥ በሚወለዱ ህጻናት ላይ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ የዘረመል ለውጦች መታየታቸውን የገለጸ ሲሆን፤ ይህንን ክስተት ‹‹እጅግ አሳሳቢ›› ሲል ጠርቶታል።
ኤጀንሲው እንዳለው፤ ከመጋቢት ወር ጀምሮ ምግብና መድኃኒትን ጨምሮ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ላይ እገዳው ከጠበቀ ወዲህ በክሊኒኮች የተመዘገቡ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ተጠቂዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
መግለጫው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ወሳኝ የሆኑ አቅርቦቶች እንዲደርሱ እና እየተባባሰ የመጣውን ስቃይ ለማስቆም አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ አሳስቧል ሲል ሚድል ኢስት ሞኒተር ነዉ ያስነበበዉ።
እስከዳር ግርማ
ሐምሌ 8 ቀን 2017 ዓ.ም
