ሩሲያ ከዩክሬን ጋር በ50 ቀናት ዉስጥ የተኩስ አቁም ሥምምነት ካላደረገች ዩናይትድ ስቴትስ በሩሲያና በንግድ ተሻራኪዎቿ ሸቀጦች ላይ ተጨማሪ ግብር እንደምትጥል ትራምፕ ትናንት አስጠንቅቀዋል።
ትራምፕ ከሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) ዋና ፀሐፊ ማርክ ሩተ ጋር ሆነዉ በሰጡት መግለጫ ሩሲያ በተቆረጠላት ጊዜ ሥምምቱንት ካልተፈራረመች ከሩሲያ ሸቀጥ በሚገዙ ሐገራት ሸቀጦች ላይ ዩናይትድ ስቴትስ 100 በመቶ የግብር ጭማሪ ትጥላለች።
ትራምፕ ከማስጠንቀቂያዉ በተጨማሪ ዩናይትድ ስቴትስ በNATO በኩል ለዩክሬን ጦር መሳሪያ እንደምትልክ አስታዉቀዋልም።ለዩክሬን የሚላከዉን የጦር መሳሪያ ዋጋ ግን የአዉሮጳ ሐገራት ይከፍላሉ።
የፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ቃል አቀባይ ዲምትሪ ፔሽኮቭ ትራምፕ ዩክሬን ለማስታጠቅ መወሰናቸዉ ጦርነቱን ለተጨማሪ ጊዜ ከማራዘም በስተቀር «የሚፈይደዉ የለም» ብለዋል።
የቀድሞዉ የሩሲያ ፕሬዝደንት ድሚትሪ ሜድቬዴቭ ደግሞ የትራምፕን ማስጠንቀቂያ «ቲያትራዊ ቀነ-ገደብ» በማለት ነቅፈዉታል።
ሜድሜዴቭ በX ገፃቸዉ በእንግሊዝኛ በፃፉት መልዕክት ሩሲያ ለትራምፕ ማስጠንቀቂያ «ደንታ የላትም» ብለዋልም።
የሞስኮ መሪዎች የዩክሬኑን ጦርነት በሰላማዊ ድርድር ለማወገድ ዝግጁ መሆናቸዉን በተደጋጋሚ አስታዉቀዋል።
የሩሲያ ምክትል የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ርያብኮቭ ዛሬ በሰጡት መግለጫም መንግሥታቸዉ ለድርድር ዝግጁ መሆኑን በድጋሚ አስታዉቀዋል።
ትራምፕ የሰጡትን ቀነገደብ ግን ምክትል የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሩ «ሩሲያ ለቀነ-ገደብ አትገዛም« በማለት ዉድቅ አድርገዉታል።
ሐምሌ 8 ቀን 2017 ዓ.ም
