የሳይበር ደህንነት ላይ ትኩረት አድርጌ እየሰራሁ ነው ገዳ ባንክ፡፡

ገዳ ባንክ እንደ ባንክ ወደ ዘርፉ ከተቀላቀለ ሁለት አመት እንዳለፈዉ የገለጸ ሲሆን በዋናነትም፣በቴክኖሎጂ፣በሳይበር ደህንነት፣ቅርንጫፎችን በማስፋፋት እና ከዲያስፖራው ማህበረሰብ ጋር ግንኙነትን መፍጠርን የተመለከቱ ስራዎች ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጻል፡፡

ባንኩ ይህን የገለፀው ወደ ስራ በሙሉ አቅሙ ከገባ ሁለት አመት ማስቆጠሩን የገለፀው የስራ አፈፃፀሙን አስመልክቶ በዛሬው እለት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው መግለጫ ነው።

የገዳ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወልዴ ቡልቶ፤ባንኩ በርካታ የኢኮኖሚ ስርዓት ለውጦችን ተቋቁሞ እድገት አስመዝግቧል ያሉም ሲሆን በበጀት ዓመቱ 575 ሚሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ገልጸዋል፡፡

በዘንድሮ በጀት አመት የተገኘው ገቢ ካለፈው ጋር ሲነፃፀር የ206 በመቶ እድገት አለውም ብለዋል።

ስራ አስፈፃሚው አቶ ወልዴ የባንኩ አጠቃላይ ሀብቱ 10 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር መሆኑን ገልጸዉ፤80 በመቶ አጠቃላይ ሀብቱ ማደጉን እና የተቀማጭ ገንዘቡም 7 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር መድረሱን ተናግረዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ባንኩ 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ለደንበኞቹ ብድር መስጠቱንም አንስተዋል።

አሁን ላይ ገዳ ባንክ በሀገር አቀፍ ደረጃ ቅርንጫፎቹን ከ100 በላይ በማድረስ ለ1ሺህ600 ሰራተኞች የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን 825 የሚሆኑት ቋሚ ሲሆኑ ሌሎቹ በኮንትራት መልክ ይሰራሉ ነው የተባለው።

በቅርቡ የባንክ ኢንዱስትሪዉን የተቀላቀለዉ ገዳ ባንክ አገልግሎቱን ተመራጭ እና ተደራሽ ለማድረግ ‹ማህበረሰብ ተኮር የባንክ ሞዴል› ወይንም ኮሚኒቲ ባንክ ሞዴል እየተጠቀመ መሆኑን ገልጿል፡፡

ልኡል ወልዴ

ሐምሌ 10 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *