የኒጀር ባለስልጣናት በቅርቡ በሀገሪቱ አጋዴዝ ክልል በሚባል ቦታ በተገኘ የከበረ ድንጋይ ሽያጭ ላይ ምርመራ መክፈታቸዉን ገልጸዋል።
ባለስልጣናቱ ይህ የተገኘው የሰማይ ዓለት ሽያጭን እያጣሩ መሆናቸውን ገልጸው፤ጉዳዩ ሕገ-ወጥ ዓለም አቀፍ ዝውውር ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
ይህ ዓለት በምድር ላይ ከተገኙት የማርስ ቁርጥራጮች ትልቁ ሲሆን፤ ባለፈው ሳምንት በኒውዮርክ በተካሄደ ጨረታ ከ5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተሽጧል።
ኒጀር ከዚህ በፊት በ2023 የተገኘውን ተመሳሳይ የማርስያን ሜትሮይት ሽያጭ ላይ በድጋሜ ምርመራ እከፍታለሁም ብላለች።
መንግሥት በሕዝብ ቴሌቪዥን ባስተላለፈው መግለጫ፤ የማዕድን፣ የከፍተኛ ትምህርትና የፍትሕ ሚኒስትሮች ይህን ጉዳይ እንዲመረምሩት መመሪያ መስጠቱን አስታውቋል።
25 ኪሎ ግራም የሚመዝነው ይህ ቀይ፣ ቡናማና ግራጫ ቀለም ያለው ዓለት በምድር ላይ ከተገኘው ሁለተኛው ትልቁ የማርስ ቁራጭ በ70 በመቶ ገደማ የሚበልጥ ነው፡፡
ዓለቱ የተገኘው በፈረንጆቹ 2023 በኒጀር አጋዴዝ ክልል ውስጥ በአንድ የሰማይ ዓለት አዳኝ አማካይነት ነው።
እስካሁን ግን የገዛው ማንነት አለመታወቁን መረጃዎች ያሳያሉ ሲል የዘገበዉ አፍሪካ ኒዉስ ነዉ።
ኤርሚያስ ገረመዉ
ሀምሌ 14/2017 ዓ.ም
