የመንግስት የሚዲያ ቢሮ በሰጠው መግለጫ ፤ የእስራኤል ወረራ የሕፃናት የጡት ምትክ ወተት ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ በመከልከሉ በጋዛ ሰርጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ጨቅላ ሕፃናት ለከፍተኛ የሞት አደጋ ተጋልጠዋል ብሏል።
እስራኤል ለ1መቶ50 ቀናት ያህል የሕፃናት የጡት ምትክ ወተት ወደ ጋዛ እንዳይገባ በመከልከሏ በሺዎች የሚቆጠሩ ጨቅላ ሕፃናትን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል ታይቶ የማይታወቅ የሰብዓዊ ቀውስ አፋፍ ላይ ትገኛለች ነዉ የተባለዉ።
ቢሮው የጋዛ የድንበር ማቋረጫዎች በአስቸኳይ እና ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲከፈቱ እንዲሁም የሕፃናት የጡት ምትክ ወተት እና ሌሎች ሰብዓዊ እርዳታዎች በአፋጣኝ እንዲገቡ ጠይቋል።
በዚህ ስልታዊ እገዳ ምክንያት ለሚጠፋው እያንዳንዱ ንጹህ ህይወት እስራኤል፣ ደጋፊዎቿ እና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ‹‹ሙሉ ሀላፊነቱን ይወስዳሉ›› ሲል ቢሮው ገልጿል።
እስራኤል በጋዛ ላይ ለ18 ዓመታት እገዳ የጣለች ሲሆን፤ ከሚያዚያ 2 ጀምሮ ሁሉንም መተላለፊያዎች በመዝጋት በክልሉ ያለውን የሰብዓዊ ሁኔታ አባብሳለች።
የጋዛ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ መሰረት ከጥቅምት 2023 ጀምሮ 1መቶ47 ፍልስጤማውያን፤ከእነዚህ ውስጥ 88 ህፃናት በረሃብ እና በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሞተዋል ሲል አናዶሉ ዘግቧል።
እስከዳር ግርማ
ሐምሌ 22/2017 ዓ.ም
