ላለፉት 27 ዓመታት የበጎ አድራጎት ተግባራትን በማከናወን የሚታወቀው የጤና፣ ልማትና ፀረ ወባ ማህበር ዜጎችን ታሳቢ ያደረገ “ለወገን የተሰኘ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም”በዛሬው እለት ስራ አስጀምረዋል።
ተቋሙ ከፍተኛውን ድርሻ ማለትም
50 በመቶ ድርሻ በመያዝ የፋይናንስ ተቋሙን ማቋቋሙን አስታውቋል።
የ”ለወገን አነስተኛ የፋይናስ ተቋም” የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ይርጋ ተስፋዬ ፤ወገን አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም የተቋቋመበት ዋነኛ አላማ በግብርና በትራንስፖርት እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ ዜጎች የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ ነው ብለዋል።
ለወገን አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም ሲቋቋም 39.3 ሚሊዮን የተፈረመና 10.3 ሚሊዮን የተከፈለ ካፒታል ነበር ያሉት የቦርድ ሰብሳቢው አቶ ይርጋ፤ አሁን ላይ የተከፈለ ካፒታሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ 21.6 ሚሊዮን ብር ማድረሱን ገልጸዋል።
የቦርድ ሰብሳቢው ለተቋሙ መቋቋም መሰረት የሆነን በ2011 ዓ/ም የወጣው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2019 ነው ያሉ ሲሆን ፤አዋጁ የበጎ አድራጎት ማኅበራት ትርፍ ማስገኘት በሚችሉ ተግባራት ላይ እንዲሰማሩ የሚፈቅድ ነው ሲሉ አንስተዋል።
ሆኖም በዛሬው እለት በይፋ ስራ መጀመሩን ያስታወቀው ተቋሙ ከዚህ በኋላ በሁሉም ክልሎች ቅርጫፎች በመክፈት የተቋቋመበትን አላማ እንደሚያሳካ አስታውቋል።
በ1990 ወደ ስራው የገባው የጤና ልማትና ፀረ ወባ ማኀበር በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ በወባ መከላከልና መቆጣጠር ከፍተኛ ስራ እየሰራ የሚገኝ ሀገር በቀል የሲቨል ማህበረሰብ ድርጅት ነው።
ልኡል ወልዴ
ሐምሌ 28/2017 ዓ.ም
