ኢትዮጵያ በአየር ንብረት መዛባት ላይ ያላት አሉታዊ ሚና ለዜሮ የተጠጋ ማለትም፣ በመቶኛ ዜሮ ነጥብ ዜሮ አራት ብቻ ቢሆንም የገፈቱ ቀማሽ መሆኗን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ይህ የተገለፀው ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ አስመልክቶ የቅድመ ጉባኤ ኤግዚቢሽን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ግቢ በተከፈተበት ወቅት ነው። የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር የአየር ንብርት ለውጥ በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ጥፋቶችን እያደረሰ መሆኑን አንስተዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ መከሰቱ የተዛባ የዝናብ ወቅት፣ ስርጭትና መጠን እንዲኖር አድርጓል ብለዋል። ይህም በዝናብ ላይ በተመሰረተው የሀገሪቱ ግብርና ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ በመሆኑ በኢኮኖሚው ላይ ጫና እንደሚፈጥር ዶ/ር ሱልጣን ወሊ አስረድተዋል።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ የተራዘመ የጎርፍ አደጋ እየተከሰተ ይገኛል ያሉ ሲሆን፣ የጎርፍ አደጋ ድግግሞሽ፣ የድርቅ፣ የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር ውሃ መቀነስ እያስከተለ ነው ሲሉ ተናግረዋል። የስነ ህይወት መመናመን፣ የግብርና ምርት መቀነስ፣ የሰብል ውድመት የመሳሰሉት ሌሎቹ ሚኒስቴር ዴኤታው የጠቀሷቸው ችግሮች ናቸው።
ከምንም በላይ የአየር ንብረት መዛባት የሰዎችን ለበሽታ የመጋለጥ ዕድል እንዳሰፋው የተናገሩ ሲሆን፣ በተለይም የወባ ወረርሽኝ እንዲጨምር አድርጓል ብለዋል። የአየር ንብረት ለውጥ የማይነካው ዘርፍ የለም፤ ሁሉም በጋራ ሊሰራበት ይገባል ሲሉም አክለዋል።
በአዲስ አበባ የሚካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤም አፍሪካውያን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በተመለከተ ድምጻቸውን በጋራ የሚያሰሙበት እንደሆነ ነው ሚኒስቴር ዴኤታው የተናገሩት።
አዲስአለም አበበ
ነሐሴ 7/2017 ዓ.ም
