የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ ያወጣውን ደንብ በጣሱ 3መቶ92 የንግድ ተቋማት ላይ የማሸግ እና የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እርምጃዎችን መውሰዱን ንግድ ቢሮው አስታውቋል።
የቢሮው ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ ብርሀኑ፤ የንግድ ተቋሙ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑን የሚያሳይ በመብራት የሚሰራ ምልክት በግልጽ በሚታይ መልኩ ያላስቀመጡ 95 ነጋዴዎች ላይ የቅጣት ውሳኔ መተላለፉን ተናግረዋል።
በምሽት ክፍለ ጊዜ የመግቢያ በሩን ዝግ በማድረግ አገልግሎት በሰጡ እና ዘግተው በጠፉ 2 መቶ 97 ነጋዴዎች ላይ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እና የማሸግ እርምጃዎች ተወስዷል ብለዋል።
አቶ አሸናፊ፤ደንቡ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ከነጋዴው ማህበረሰብ ጋር ሰፊ ውይይት መደረጉን አንስተዋል።
የመብራት መቆራረጥ ፣የትራንስፖርት ችግር እና የፀጥታ ስጋት እንዴት ይቀረፋሉ የሚሉ ጥያቄዎች ከነጋዴው መነሳታቸውንም አስታውሰዋል።
ንግድ ቢሮው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ስራዎች መስራቱን ያነሱት አቶ አሸናፊ፤ ለአብዛኞቹ ችግሮች መፍትሄ መሰጠቱን ገልፀዋል።
በደንቡ መሰረት በአዲስ አበባ የሚገኙ ንግድ ቤቶች እና የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎች እስከ ምሽት ሶስት ተኩል እና አራት ሰዓት አገልግሎት መስጠት ይኖርባቸዋል።
በምሽት ክፍለ ጊዜ የንግድ ተቋሙ የመግቢያ በሩን ዝግ በማድረግ አገልግሎት የሚሰጥ ከሆነ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑን የሚያሳይ በመብራት የሚሰራ ምልክት በግልጽ በሚታይ ቦታ ላይ ማስቀመጥ እንደሚኖርበት በደንቡ ላይ መስፈሩን ተመልክተናል።
አቤል እስጢፋኖስ
ነሐሴ 26/2017 ዓ.ም
