የሕዳሴ ግድብን ግንባታ በማስጀመራቸው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሊመሰገኑ ይገባል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር )

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጳጉሜ 4/2017 ዓ.ም. ይመረቃል ተብሎ የሚጠበቀውን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ግንባታ በማስጀመራቸው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የጉባ ላይ ወግ” በተሰኘ እና በብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሰኞ ነሐሴ 26/2017 ዓ.ም. በሚኒስትር ማዕረግ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪያቸው ከሆኑት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጋር ባደረጉት ውይይት ወቅት ነው ምስጋናቸውን ያቀረቡት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢትዮጵያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በ2003 ዓ.ም. ወቅቱ በሁሉም ዘርፍ ምቹ መሆኑን ተገንዝበው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በማስጀመራቸው ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።

ይሄም ከአንድ አገር መሪ የሚጠበቅ ተግባር ተደርጎ መገለጽ እንዳለበት የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይኹን እንጂ እርሳቸው ግድቡ በተጀመረ በዓመቱ በማለፋቸው በወቅቱ የግንባታ ዝግጅት ምዕራፍ ላይ እንደነበር ተናግረዋል።

“ያም ቢሆን ግን ለማስጀመራቸው ከፍተኛ ዋጋ ሊሰጠው ይገባል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቀጣይነት ከእርሳቸው ሥልጣኑን የተረከቡትን ኃይለማርያም ደሳለኝንም አመስግነዋል።

ከ14 ዓመት በፊት ኢትዮጵያ በታላቁ የዓባይ ወንዝ ላይ ከአፍሪካ ቀዳሚ ከዓለም ደግሞ ተጠቃሽ የሆነ ግዙፍ ግድብ መገንባት መጀመሯን በማብሰር በይፋ የመሠረት ድንጋዩን በማስቀመጥ ግንባታውን ያስጀመሩት የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ነበሩ።

ከእርሳቸው በመቀጠል አገሪቱን ማስተዳደር የጀመሩት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም ቢሆኑ ግድቡን ከተረከቡበት ጊዜ ጀምሮ “እየተንገዳገደ የተወሰነ ቦታ እንዲደርስ ስላደረጉት ጥረት” ምስጋና እንደሚገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናግረዋል።

ነሐሴ 27/2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *