ባለስልጣኑ በቅርቡ ለሚከበሩት የሃይማኖት እና ሀገራዊ በዓላት እንዲሁም አዲስ አበባ ውስጥ ለሚካሄዱት የተለያዩ አለምአቀፍ ጉባኤዎች ትኩረት ሰጥቶ የቁጥጥር ስራውን አጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቋል ።
በበዓል ሰሞን የገበያ ቁጥጥር፤ ለበዓላት የሚቀርቡ የምግብና መጠጥ ምርቶች ጥራት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ነው ተብሏል።
በዚህም በአያያዝ ችግር የተበላሹ ወይም የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ምርቶችን ሲሸጡ የተገኙ 85 ተቋማት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ገልጿል ።
በተጠናቀቀው በጀት አመትም ባለሥልጣኑ ባደረገው የቁጥጥር ዘመቻ ፤ ህገወጥ መድኃኒት ሽያጭና ዝውውር፣ስታንዳርዳቸውን ያልጠበቁ መድኃኒቶችን በግልጽ በሽያጭ ላይ ያዋሉ ፣ ያለ ፈቃድ መድኃኒቶችን ሲያዘዋውሩና ሲሸጡ የተገኙ አካላት ተለይተው አስፈላጊው ህጋዊ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ተጠቅሷል
እንዲሁም ደረጃቸውን ያልጠበቁ የምግብ ማምረቻ እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣የምግብ ዝግጅት እና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የንፅህና ጉድለት የታየባቸው፣ ያለፈቃድ ሲሰሩ የተገኙ ተቋማት ላይም ማስተካከያ እንዲያደርጉ ትእዛዝ ተሰጥቷል ተብሏል።
ህብረተሰቡም የሚገዛውን ምግብ እና መድኃኒት ፈቃድ ካላቸውና ህጋዊ ከሆኑ ተቋማት መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለበት እና የሚያሳስብ ነገር ሲያጋጥም ወዲያውኑ በ8864 እንዲያሳዉቁ የሚል ጥሪውን ባለስልጣናኑ አቅርቧል።
ሐመረ ፍሬው
ነሐሴ 30/2017 ዓ.ም
