ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ሀገር ብትሆንም ከቡና ምርት የምታገኘው ምርት እጅጉን አነስተኛ እና ስሟን የማይመጥናትን ነበር ሲሉ የግብርና ሚኒስትሩ ገለፁ ።
የግብርና ሚኒስትር አቶ አዲሱ አረጋ ይህን ያሉት በምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ገሼ አከባቢ በቀርጫንሼ ግሩፕ ፤ያለጥላ በ750ሄክታር መሬት ላይ እየለማ ያለውን የቡና ምርት በጎበኙበት ወቅት ነው።
በዚሁ ወቅት ሚኒስትሩ ያለጥላ የሚከወን የቡና ልማት የኢትዮጵያን የቡና ምርትና ንግድ ለማሳደግ ይረዳልም ብለዋለ።
የቀርጫንሼ ግሩፕ መሥራችና ባለቤት እስራኤል ደገፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው ፤የቡናን‹‹ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰራ ስራ በሄክታር አንድ ኩንታል ብቻ ይገኝ የነበረውን ቡና ወደ 56 ኩንታል ማሳደግ መቻሉን አስታውቀዋል።
መስራቹ ቡናን ኋላቀር ከሆነ አመራረት በማውጣት ሀገሪቷ በተፈጥሮ ከምታገኘው ፀጋ ባለፈ፤ ለምርታማነት አስፈላጊ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ከእስራኤል እንዲሁም አግሮኖሚስቶችን ከብራዚል በማምጣት ሰፋፊ ሥራዎችን እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም በዓዲስ የአመራረት ዘዴ ቡናን ከዘለማድ አሰራር በማላቀቅ በቂ አየርና የፀሐይ ብርሃን እንዲያገኝ በማስቻል ያለ ጥላ በማልማት ላይ እንደሚገኙና ለተመዘገበው ውጤትም ይህ አሰራር አንዱ ምክንያት መሆኑን አቶ እስራኤል ተናግረዋል።
ሆኖም ድርጅቱ በይርጋጨፌ፣ በጉጂና በጅማ ዞን በሚገኙ የእርሻ ቦታዎቹ ላይ ይህን አሰራር ተግባራዊ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የግብርና ሚኒስትሩ በዓለም የቡና ገበያ ውጤታማ የሆነውን ያለጥላ ቡና የማልማት ሥራ ማጠናከር ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
መንግሥት ለቡና ልማት ሥራው ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
ይህ ቀርጫንሼ ግሩፕ የተጠቀማቸው ዘር፣ማሽን እና ጥናት ከዚህ ቀደም ይባክ የነበረውን ቡና በመታደግና አሰራሩን በቴክኖሎጂ በማስተሳሰር የኢትዮጵያን የቡናን ታሪክ እንደ አዲስ የሚፅፍ ነው” ሲሉም ገልጸዋል።
ልኡል ወልዴ
ጳጉሜ 3/2017 ዓ.ም
