የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እስራኤል በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ በሚገኘው የሃማስ መሪዎች ላይ የሚሳኤል ጥቃት ካደረሰች ከጥቂት ቀናት በኋላ እስራኤል መድረሳቸውን i24 ኒውስ ዘግቧል።
ሩቢዮ ከጉዞው በፊት በኤክስ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ፤ወደ እየሩሳሌም እየሄድኩ ነው። ትኩረቴ ታጋቾችን ማስመለስ፣ ሰብዓዊ እርዳታ ለሲቪሎች መድረሱን ማረጋገጥ እና በሃማስ የሚሰነዘረውን የጥቃት ስጋት መፍታት ላይ ይሆናል ብለዋል።
እስራኤል ማክሰኞ ዕለት በዶሃ የሚገኙ የሃማስ መሪዎች ይኖሩበት በነበረ የመኖሪያ ግቢ ላይ በሰነዘረችዉ ጥቃት አምስት የሃማስ አባላት እና አንድ የኳታር የጸጥታ መኮንን ተገድለዋል።
ኳታር ከግብፅ እና ከአሜሪካ ጋር በመሆን በሃማስ እና በእስራኤል መካከል በጋዛ የእስረኛ እና ታጋች ልውውጥ እንዲሁም የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ በሚደረገው ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድር ተሳታፊ ነች፡፡
እስራኤል 48 ዜጎቿ አሁንም በጋዛ ታግተው እንደሚገኙ ትገምታለች፤ ከእነዚህም መካከል 20ዎቹ በህይወት ያሉ ናቸዉ ተብሏል ሲል የዘገበዉ አልጀዚራ ነዉ፡፡
እስከዳር ግርማ
መስከረም 5/2018 ዓ.ም
