የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን በ2018 ዓ.ም ህዳር መጨረሻ ለመጀመር እቅድ መያዙን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው፤ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የኢትዮጵያን የአቪየሽን ኢንዱስትሪ ወደ ላቀ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረው አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም አፍሪካውያንን ከመላው ዓለም ጋር ለማገናኘት ፣ቱሪስቶች እና ኢንቨስተሮችን ለመሳብ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡
አውሮፕላን ማረፊያው አየር መንገዱ በአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት እየተጫወተ ያለውን ግንባር ቀደም ሚና የበለጠ እንደሚያሳድገው ተናግረዋል፡፡
ዋና ስራ አስፈጻሚው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን ለመጀመር የሚያስችሉ ዝግጅቶች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን አንስተዉ፤ ግንባታዉን በህዳር ወር መጨረሻ ለመጀመር እቅድ መያዙን አመላክተዋል።
መስከረም 8/2017 ዓ.ም
