ትራምፕ ከኔታንያሁ ጋር በሚያደርጉት ንግግር የጋዛን የሰላም እቅድ ለማቅረብ ጥረት ያደርጋሉ ተባለ

ዶናልድ ትራምፕ ዛሬ የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን በዋይት ሀውስ ያስተናግዳሉ፡፡

በርካታ የምዕራባውያን መሪዎች የአሜሪካንና የእስራኤልን ተቃውሞ በመጻረር የፍልስጤምን መንግስትነት በተቀበሉ ማግስት የሚደረገዉ ይህ ስብሰባ፤ በጋዛ ሰላም እንዲወርድ የሚደረጉ ጥረቶችን ይደግፋል ተብሏል፡፡

ኔታንያሁ ትራምፕ በጥር ወር ወደ ስልጣን ከተመለሱ በኋላ ለአራተኛ ጊዜ ነዉ ይህንን ጉብኝት የሚያደርጉት፡፡

ሀገራቸው ከሀማስ ጋር በጋዛ ሰርጥ የምታደርገው ጦርነት ሁለት ዓመት ሊሞላው ሲቃረብ እያደገ የመጣውን ዓለም አቀፍ መገለል እየተጋፈጠች ባለችበት በዚህ ወቅት፤ የሀገራቸውን እጅግ ጠቃሚ ግንኙነት ለማጠናከር በመፈለግ ወደ አሜሪካ መጓዛቸዉ ተገልጿል፡፡

ኔታንያሁ ባለፈው ሳምንት ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ እና ሌሎች በርካታ ሀገራት የፍልስጤምን መንግስትነት እውቅና ለመስጠት የወሰዱትን እርምጃ ‹‹አሳፋሪ ውሳኔ›› ሲሉ በብርቱ አውግዘዋል።

እነዚህ ሀገራት ለእስራኤል-ፍልስጤም ግጭት የሁለት መንግስታት መፍትሄ የማግኘት ተስፋን ከፍ ለማድረግ እና ጦርነቱን ለማቆም እንዲህ አይነት እርምጃ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከሮይተርስ ጋር በነበራቸዉ ቆይታ እውቅና የመስጠት እንቅስቃሴዎችን ለሀማስ የተሰጠ ሽልማት ሲሉ የነቀፉት ትራምፕ፤በፍልስጤም ግዛት ያለውን ጦርነት ለማቆም እና በሀማስ የተያዙትን የቀሩ ታጋቾችን ለማስለቀቅ ከኔታንያሁ ጋር ስምምነት ላይ እንደምንደርስ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡

ትራምፕ ከሮይተርስ የዜና ወኪል ጋር በነበራቸዉ የስልክ ቃለ ምልልስ፤ ኔታንያሁን በቅጽል ስማቸዉ በመጥራት ቢቢም ስምምነት ማድረግ ስለሚፈልግ በጣም ጥሩ ምላሽ እያገኘን ነው ፤ ሁሉም ሰው ስምምነት ማድረግ ይፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የሳውዲ አረቢያ፣ ኳታር፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣ ዮርዳኖስ እና ግብፅ መሪዎችን ላደረጉት ድጋፍ አመስግነው፤ ስምምነቱ ከጋዛ ባለፈ ሰፋ ያለ የመካከለኛው ምስራቅ ሰላምን ያለመ ነው ብለዋል።

በጋዛ የሰላም ሁኔታ ዙሪያ ስምምነት ላይ መደረሱን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸዉ አንድ ከፍተኛ የእስራኤል ባለስልጣን፤ ኔታንያሁ ሰኞ ከትራምፕ ጋር ሲገናኙ እስራኤል ለእቅዱ የምትሰጠውን ምላሽ ያቀርባሉ ብለዋል ሲል የዘገበዉ ሮይተርስ የዜና ወኪል ነዉ።

እስከዳር ግርማ

መስከረም 19/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *