”ደጋግ እጆች ለልጆች” የሚል መሪ ቃልን ያነገበው የሩጫው መርሀ ግብርን ደጋግ ልቦች እንዲሳተፉበት ተጠይቋል፡፡
መስከረም 29 የሚከበረውን አለም አቀፍ የልብ ቀንን ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል ህዳር 30 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄድ የሩጫ መርሀ ግብር እንዳዘጋጀ አስታውቋል ።
መርሀ ግብሩ ጠዋት 4 ሰአት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ በሚገኘው ከኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል መነሻውን አድርጎ በሜክሲኮ ለገሀር እንዲሁም በብሔራዊ አድርጎ በኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ የልብ ማእከል ይጠናቀቃል።
የተቋሙ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ህሩይ አሊ በመግለጫው ላይ እንደተናገሩት በአሁኑ ሰአት በማዕከሉ ከ 8ሺ በላይ ህፃናት ወረፋ በመጠበቅ ላይ ይገኛሉ።
በየአመቱ 1ሺ 3 መቶ ያህል አዳዲስ ታካሚዎች ወደ ተቋሙ ይመጣሉም ብለዋል።
በተጨማሪም 12ሺ ታካሚዎች በተመላላሽ ክፍል እንደሚስተናገዱ እና በአመት ለ650 ታካሚዎች በቀዶ ህክምና እንዲሁም በደም ስር የሚሰጥ የልብ ህክምና(cathlab) አገልግሎትን እንደሚሰጥ የተቋሙ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ኤሌዘር ሀይሌ አብራርተዋል።
ማእከሉ ከሚሰጠው የህክምና አገልግሎት ሌላ የህፃናት እድገት እና ትምህርት ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማበርከቱም ተነግሯል፡፡
ህዳር 30 ቀን 2018 አ.ም በሚደረገው የሩጫ መርሀ ግብር የሚሰበሰበው ገቢም ሙሉ ለሙሉ ለኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል እንደሚውል ከተቋሙ ጋር በአጋርነት የሚሰራው jloord የማስታወቂያ ድርጅት ሀላፊ የሆኑት አቶ ፋሲካ ገብሬ አሳውቀዋል።
የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማእከል ላለፉት 36 አመታት ከ 9ሺ በላይ ለሆኑ ታካሚዎች ነፃ የልብ ቀዶ ህክምና አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ፣ ለትርፍ ያልተቋቋመ እና ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ለሚመጡ ታካሚዎች ከክፍያ ነፃ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም መሆኑ ተገልጿል ።
ሀና ሰይፉ
መስከረም 19/2018 ዓ.ም
