የአደባባይ በዓላት ማህበረሰቡ ለሀገር በቀል ልብሶች ያለውን ፍላጎት አሳድጎታል ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህልና ትምህርት ቁርኝት ተመራማሪ ዶ/ር ታደሰ ጃለታ ተናገሩ።
ዶ/ር ታደሰ ከኢትዮ ኤፍ አም ጋር በነበራቸው ቆይታ የአደባባይ በዓላት ከጥንት ጀምሮ የነበሩ ባህሎችን ከሀገር በቀል አልባት ጋር በማጣመር ለሚቀጥለው ትውልድ መሸጋገሪያ ድልድይ ናቸው ሲሉም አስረድተዋል።
አሁን ያለው አዲሱ ትውልድ ሁሉን የቤተሰቡን ባህልና እሴት ያውቃል ማለት አይቻልም ብለዋል።
ሆኖም በእነዚህ በዓላት ዜጎች የሃገራቸውን የባህል ሃብትና ፀጋ እንዲሁም አብሮ የመኖር እሴትን የሚማሩበት ነው ሲሉ አብራርተዋል ።
በተጨማሪ የአደባባይ በዓላት ኢትዮጵያ የብዘሀኑ ሃይማኖቶች፣ባህሎች እና ቱፊቶች ባለቤት መሆኗን ከሀገሪቱ አልፎ ለአለም ህዝብ ማሳያ መድረክ እንዲሁም የባህል ሽግግር መፍጠሪያ መድረክ ስለ መሆናቸውም ተናግረዋል ።
ባህል አንድ ቦታ ተቸንክሮ የሚቆም ሳይሆን በሰው ልጅ ፍላጎት በየጊዜው የሚለወጥና የሚሻሻል ነው ሲሉም ገልጸዋል።
የሰው ልጅ ፍላጎት ደግሞ በየጊዜዉ እየተሻሻለ እና እያደገ የሚሄድ ነው የሚሉት ተመራማሪው በጥንት ጊዜ እናቶችና አባቶች ሲለብሱት የነበረውን ባህላዊ መገለጫዎችን መሰረቱን ሳይለቅ በዘመናዊ መልክ እየተሻሻሉ ይገኛሉ ነው ያሉት።
ይህ መሆኑ አሁን ያለው አዲሱ ትውልድ ከምዕራባዊያን ሰልባጅ ይልቅ የባህል ልብሶችን ሳይጠላ የበለጠ እየወደደና እየተቀበለ እየመረጠ መጥቷል ሲሉ ገልፀዋል።
ልኡል ወልዴ
መስከረም 21/2018 ዓ.ም
