በዛሬዉ እለት የኢትዮጵያ ኡደታዊ የስነምጣኔ ሆት ስፖት 2025 በሳይንስ ሙዚየም ተከፍቷል።
የሰርኩላር ኢኮኖሚ ወይም ቆሻሻን መልሶ መጠቀም ላይ ትኩረት ያደረገዉ ይህ ሁነት የቆሻሻ አጠቃቀምን እንዲሁም አወጋገድ ስርአት ዙሪያ ያተኮረ ነዉ ተብሏል።
የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ለሊሴ ነሜ በንግግሯቸዉ ሀገራዊ ሰርኩላር ኢኮኖሚ ፍኖተ-ካርታ ይፋ መሆኑን አስታዉሰዋል።
በኢትዮጵያ ያለዉን ቆሻሻ መልሶ መጠቀም ዙሪያ ያሉ ስራዎችን ባለስልጣኑ እየደገፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በተለይም ቆሻሻን መልሶ መጠቀም ላይ የሚሰሩ መካከለኛ እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ወደዚህ እንዲገቡ እናበረታታለን ብለዋል።
በተለይም ባለድርሻ የሆኑ የግሉ ዘርፍ አካላት የሚያስፈልጉ የፋይናንስ እና የቴክኒክ ድጋፎችን በማድረግ ማገዝ እንደሚጠበቅባቸው ባለስልጣኑ ገልፆል።
ዛሬ የማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ በተካሄደው የኢትዮጵያ ኡደታዊ ስነምጣኔ ሆት ስፖት 2025 መድረክ ቆሻሻን በአግባቡ መያዝ ብቻ ሳይሆን ስራ እድል ለመፍጠር ፣ለኢኮኖሚን እድገት ፣ሙቀት አማቂ ጋዞችን ለመቀነስ እንደሚያስችል ተገልፆል።
ከአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ ፖሊሲ አውጪዎች፤ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት፤ የኢንደስትሪ ተቋማት፤ የፈጠራ ባለሙያዎች በማስጀመርያ ስነስርዓቱ ታድመዋል።
ቁምነገር አየለ
መስከረም 21/2018 ዓ.ም
