ከጋዛ የሰላም ስምምነት በኋላ ጣሊያን ለፍልስጤም የአገርነት ዕዉቅና ለመስጠት መቃረቧን በጠቅላይ ሚኒስትሯ በኩል ገለጸች

በግብጽ ከተካሄደዉ ስብሰባ በኋላ ጣሊያን የራሷን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ ናት ሲሉ ጆርጂያ ሜሎኒ ተናግረዋል፡፡

ዕቅዱ ተግባራዊ መሆን ከቻለ የጣሊያን ለፍልስጤም የአገርነት ዕዉቅና የመስጠት ሀሳብ ሩቅ አይሆንም ሲሉ በግብጽ በሻርም ኤል-ሻይክ ስብሰባ ላይ ለተገኙ ጋዜጠኞች መናገራቸዉ ተዘግቧል፡፡

ጣሊያን የፍልስጤምን የአገርነት ግንባታ በመደገፍ ለጋዛ ነዋሪዎች የምታደርገዉን ሰብዓዊ ድጋፍም እንደምትቀጥል አስታዉቀዋል፡፡

ጣሊያን የበኩሏን ለማድረግ ዝግጁ ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሯ፤ ይህ ትልቅ ዕድል ነዉ፣ ታሪካዊ ቀንም ጭምር ነዉ፣ ጣሊያን የዚህ አካል በመሆኗ ኩራት ይሰማኛል ብለዋል፡፡

በሃማስ እና እስራኤል መካከል የተፈረመዉ የሰላም ስምምነት ለዶናልድ ትራምፕ ትልቅ ስኬት ነዉ ሲሉ ያሞካሹት ሜሎኒ፤ በዩክሬንም ይህ ስኬት እንዲገጥማቸዉ እመኛለሁ ብለዋል፡፡

ዓርብ ዕለት መተግበር የጀመረዉ የመጀመሪያ ዙር የሰላም ስምምነት፤ሁሉም የእስራኤል ምርኮኞች በፍልስጤም እስረኞች ምትክ እንዲፈቱ እና የእስራኤል ኃይሎች በሂደት ከጋዛ ሰርጥ ሙሉ ለሙሉ እንዲወጡ የተስማሙበት ነዉ፡፡

የዕቅዱ ሁለተኛ ምዕራፍ ደግሞ በጋዛ አዲስ የአስተዳደር ዘዴ መመስረት፣ ሁለገብ ኃይል ማቋቋም እና ሃማስን ትጥቅ ማስፈታት የተካተተበት ነዉ፡፡

ሃማስ ትናንት በጋዛ ሰርጥ የሚገኙትን 20 እስራኤላዊያን ምርኮኞችን በሙሉ ከለቀቀ በኋላ፤ በእስራኤል እስር ቤቶች ታስረው የነበሩ ፍልስጤማውያን መፈታት መጀመራቸዉ ተገልጿል፡፡

እስከዳር ግርማ

ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *