የተባበሩት መንግስታት ቃል አቀባይ፤እስራኤል ወደ ጋዛ የሚገቡትን የጭነት መኪናዎች ቁጥር እንደምትቀንስ ማሳወቋን ተናግረዋል።
የእስራኤል ባለስልጣናት እስካሁን በተለቀቁት የሟች ታጋቾች ብዛት የተነሳ ወደ ጋዛ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው የሰብዓዊ ድጋፍ መኪኖች ቁጥር እንደሚቀንስ ወይም እንዲዘገይ ለማድረግ ለተባበሩት መንግስታት ማሳወቃቸውን የመንግስታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ አስታውቀዋል።
በጋዛ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ/ኦቻ/ቃል አቀባይኦልጋ ቼሬቭኮ ፤ የእስራኤል ባለስልጣናት እስካሁን ከእስር በተለቀቁት የታጋቾች ቁጥር ምክንያት የሚጠበቀው የጭነት መኪኖች ቁጥር እንዲዘገይ ወይም እንደሚቀንስ ለተባበሩት መንግስታት አሳውቀዋል ወይ የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞች ቀርቦላቸው ነበር።
ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ኦልጋ ቼሬቭኮ፤ ከእስራኤል ባለስልጣናት ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ተወያይተናል፤ በእርግጥ ተዋዋይ ወገኖች በተኩስ አቁም ስምምነቱ ውስጥ የተቀመጡትን ሀሳቦች እንዲያከብሩ ማበረታታታችንን እንቀጥላለን ብለዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል ።
ሮይተርስ ተመልክቼዋለሁ ባለዉ መረጃ መሰረት፤ እስራኤል ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከረቡዕ ጀምሮ 3መቶ የእርዳታ መኪኖች ብቻ እንደምትፈቅድ አስታዉቃለች፡፡
እስራኤል ስምምነት ላይ ከተደረሰባቸዉ ቁጥሮች ግማሹን ወደ ጋዛ እንዲገባ እንደምትፈቅድ እና ልዩ ፍላጎቶች ካልሆነ በስተቀር ነዳጅም ሆነ ጋዝ ወደ ክልሉ እንደማይገባ ተናግራለች ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ሀና ሰይፉ
ጥቅምት 05/2018 ዓ.ም
