ዜጎችን ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች እያጋለጡ የሚገኙት የታሸጉ ምግቦች ቁጥጥር እንዲደረግባቸዉ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ወጥቷል።
የዚህ አዋጅ መፅደቅ ማህበረሰቡን ተላላፊ ካልሆኑ ህመሞች በመከላከል ረገድ ጉልህ ጠቀሜታ አለው ተብሏል።
ረቂቅ አዋጁ የታሸጉ ምግቦች ሙሉ ለሙሉ ከገበያ እንዲወጡ የሚያደርግ ሳይሆን፤ ምግቦቹ በውስጣቸው የያዙትን የስኳር፣ጨውና የስብ መጠን ሁሉም ሰው እንዲረዳውና በግልጽ እንዲቀመጥ የሚያደርግ ነው።
አሁን ላይ ከዘመናዊነትና የባህል ለውጦች ጋር ተያይዞ ማህበረሰቡን ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች የሚያጋልጡ ምግቦችን አብዝቶ በመጠቀሙ ለከፍተኛ የጤና ጉዳት አልፎም ለሞት እየተዳረገ ይገኛል ነው የተባለው።
ረቂቁ የተዘጋጀው በተዋልዶ ጤና አገልግሎት ሰጪ ማህበራት ህብረት (ኮርሃ) ሲሆን፤ድርጅቱ ከ30 አመታት በላይ የዘለቀ በተዋልዶ ጤና ላይ የሚሰሩ የሃገር አቀፍና አለም አቀፍ ድርጅቶች ህብረት ነው፡፡
ድርጅቱ የማህበረሰብ ጤናን የሚመለከቱ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ይሰራል ያሉት የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ አቶ አበበ ከበደ ፤ ትኩረቱን ከሚያደርግባቸው ጉዳዮች ውስጥ ለሁሉም የጤና ጥቅሞች እንዲሁም የጤና እክሎች መነሻ የሆነው ስነ-ምግብ ወይንም አመጋገብ አንዱ ነው፡፡
ጤና ሚንስቴር ከሚመለከታቸው መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመሆን እነዚህን ምግቦች ለመቆጣጠር የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ አቅርቧል፡፡
ልዑል ወልዴ
ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም
