የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኢትዮጵያ የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎት እንዲሰጡ የተፈቀደላቸውን የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶችን ስም ዝርዝር ለሕዝቡ ይፋ አድረገ።
ባንኩ ዛሬ ህዳር 3 ቀን ባወጣው መግለጫ፣ ከ 90 በላይ ለሚሆኑ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎት እንዲሰጡ ህጋዊ ፍቃድ ማግኘታቸውን አስታውቋል።
መግለጫው፣ ቀደም ሲል የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎት እንዳይሰጥ ታግዶ የነበረው እና ዋና መሥሪያ ቤቱ በአሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት የሚገኘው ራማዳ ፔይ (ካህ) ድርጅት በሕጋዊ የገንዘብ አስተላላፊዎች ዝርዝር ውስጥ ዳግም እንዲካተት ተደርጓል ብሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዳስታወቀው፣ ውሳኔው ላይ የተደረሰው በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ አጠቃላይ ግምገማ ከተካሄደ በኋላ ነው።
መግለጫው፣ በሀገሪቱ ሕግና ደንብ መሠረት በድርጅቱ ላይ አስፈላጊው የቁጥጥር እና የክትትል ሂደት መደረጉንም ጠቅሷል።
ባንኩ አክሎም፣ በአሁኑ ጊዜ አገልግሎት እንዳይሰጡ ታግደው የሚገኙ ሌሎች የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ሁሉ የሀገሪቱን ሕግና ደንብ የሚጠይቀውን መስፈርት ለማሟላት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ አሳስቧል።
ህዳር 03 /2018 ዓ.ም
