በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በገንዘብ እጥረት ምክንያት የሕክምና እና የመከላከያ መንገዶችን ማግኘት አልቻሉም ተብሏል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የኤድስ መከላከያ ተቋም ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድጋፍ መስተጓጎል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አገልግሎቱን እንዳያገኙ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።
በዶናልድ ትራምፕ የስልጣን ዘመን ዩናይትድ ስቴትስ ይህንን የገንዘብ ድጋፍ እንድታቋርጥ ከተደረገ በኋላ ለበሽታው የሚሰጠው ዓለም አቀፍ ምላሽ ቀውስ ውስጥ መግባቱም ተነግሯል፡፡
ምንም እንኳን አንዳንድ ኤችአይቪ ቫይረስን ለመከላከል የሚረዱ ፈንዶች ቢመለሱም ነገር ግን የ(USAID) ፕሮግራሞች መቋረጥ ችግሩን እንዳወሳሰበው ተነግሯል፡፡
የተባበሩት መንግስታት እንደገለጸው ድጋፍ በመሰረዙ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ላይ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ጫናዎችን ተፈጥሯል፡፡
እነዚህ አገልግሎቶች በመቋረጣቸው ምክንያት ከኤችአይቪ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ በኤችአይቪ የመያዝ ከፍተኛ አደጋ ላይ ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችም ማግኘት የሚገባቸውን የመከላከያ መሳሪያዎችን ማግኘት አልቻሉም ተብሏል፡፡
ከ2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ታዳጊ ልጃገረዶች እና ወጣት ሴቶችም በዚህ ፈንድ አማካኝነት የሚመጡ አገልግሎቶችን ማግኘት አልቻሉም፡፡
በገንዘብ ቅነሳው ምክንያት፣ፕርኢፒ በመባል የሚታወቀውን የመከላከያ የኤችአይቪ መድሃኒት የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር በብሩንዲ በ64 በመቶ፣ በኡጋንዳ በ38 በመቶ እና በቬትናም በ21 በመቶ መቀነሱ የተነገ ሲሆን በናይጄሪያ የኮንዶም ስርጭት በ55 በመቶ መቀነሱን የአልጀዚራ ዘገባ አመላክቷል፡፡
የውልሰው ገዝሙ
ህዳር 17/2018 ዓ.ም
