ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ እናት ፓርቲ በቦርዱ ላይ ያልተገባ ተጽዕኖ ለመፍጠር ከሚያደርጋቸው ሙከራዎች ሊቆጠብ ይገባል ሲል አዲስ ባወጣው መግለጫ አስጠንቅቋል።
ቦርዱ፣ እናት ፓርቲ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ቦርዱ ፓርቲውን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል በማለት ያቀረበው ውንጀላ “መሠረተ ቢስ” እና “ሐሰተኛ” ነው በማለት አጣጥሏል።
ፓርቲው ሁሉንም ሕጋዊ ሰነዶችና የበላይ አካላቱን ውሳኔ ባለማቅረቡ የአምስት ፓርቲዎች ቅንጅት እባል እንዳይሆን ለተጣለበት እገዳ ቦርዱን መክሰሱ “ተቀባይነት የሌለው” እና ፓርቲው “ለሕግ ተገዥ” አለመሆኑን ያሳያል በማለት የወቀሰው የቦርዱ መግለጫ፣ ፓርቲው አሁንም ለሁሉም የላዕላይ ምክር ቤት አባላቱ ጥሪ አድርጎ የቅንጅቱ አባል ለመሆን አስወስኖ ሲያቀርብ ቦርዱ እንደሚያጸድቅለት ገልጧል።
ቦርዱ አያይዞም፣ የፓርቲው ውንጀላ ቦርዱ ከፋይናንስ አስተዳደር ጥሠት ጋር በተያያዘ ካኹን ቀደም ባገኘው ግኝት የፓርቲው አመራሮች በሕግ እንዳይጠየቁና ይልቁንም ከስህተታቸው እንዲማሩ አሳልፎት የነበረውን ውሳኔ መልሶ እንዲያጤነው የሚያስገድድ ነው ብሏል።
ቦርዱ የፓርቲው የቀድሞና የአሁን አመራሮች በፓርቲው አሠራርና ገንዘብ አስተዳደር ላይ ካሁን ቀደም ያቀረቧቸውን ቅሬታዎች ለመፍታት ያደረገውን ጥረት ፓርቲው ፋይዳ ቢስ አድርጎ ቆጥሯል በማለትም የቦርዱ መግለጫ ተችቷል።
ህዳር 17/2018 ዓ.ም
