ባንኮች ጀማሪ የስራ ፈጣሪዎችን ያለማስያዣ ብድር በመስጠት ማበረታታት እንደሚገባቸዉ ተገለፀ

ይህ የተገለፀው ገዳ ባንክ በማህበር ለተደራጁ ጀማሪ የስራ ፈጣሪዎች ያለምንም ማስያዣ በብድር ተሽከርካሪዎች በሰጠበት ወቅት ነው።

ተሽከርካሪዎቹ መካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች የትራንስፖርት ችግር መቀነስ የሚችል አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸውን የገዳ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወልዴ ቡልቶ ተናግረዋል ።

ባንኩ ሸገር ኢንተርፕራይዝ አሶሴሽን የተባለ ክህሎት እና የስራ ፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶችን አሰልጥኖ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያገኙ እየሰራ ነው ከተባለው ተቋም ጋር በመተባበር ነው ከአካባቢ ብክለት ነፃ የሆኑ ተሽከርካሪዎችን ወጣቶቹ እንዲያገኙ እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ነዉ ያደረግነዉ ሲሉ አቶ ወልዴ ተናግረዋል፡፡

በዚሁ ወቅት ገዳ ባንክና ናይስ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በመካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች የትራንስፖርት ችግር ለመቀነስ የሚያስችል ዘመናዊ የታክሲ አገልግሎት ለመጀመር የትብብር ስምምነትም ተፈራርመዋል።

በዚህ የጋራ ስምምነት መሠረት፣ ገዳ ባንክ አስር ዘመናዊ ተሽከርከሪዎችን በመግዛት ለናይስ ትሬዲንግ ማህበር ያስረከበ ሲሆን፣ አገልግሎቱ በቅርብ ቀን ወደ ሥራ እንደሚገቡ የናይስ ትሬዲንግ ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መስራች ዶክተር ጃለታ ሙላቱ ተናግረዋል።

ዶክተር ጃለታ እነዚህ አስራ አምስት ሰዎችን የመያዝ አቅም ያላቸው ተሽከርካሪዎች ከጥሬ ገንዘብ ነፃ በሆነ የክፍያ ሥርዓት የሚሰሩ መሆናቸዉንም አስረድተዋል።

በአሁኑ ጊዜ በ10 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት መስጠት የሚጀምሩ ሲሆን፣ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 1ሺህ ተሽከርካሪ በጋራ በማስመጣት አገልግሎቱን በስፋት ለማቅረብ ማቀዳቸውን አስታውቀዋል፡፡

ልኡል ወልዴ

ህዳር 19/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *