ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በመሬት፣በአየር ላይ እና በድሮኖች የሚደረገው ፍልሚያ ቀጥሏል ተብሏል።
በምስራቃዊ ዩክሬን በተለይም በዶኔስክ ክልል አካባቢ ውጊያው ተጠናክሮ ቀጥሏል የተባለ ሲሆን፤ የሩሲያ ጦር በአንዳንድ ስልታዊ ስፍራዎች ቀስ በቀስ ወደፊት እየገሰገሰ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ዩክሬን በበኩሏ የመከላከያ መስመሮቿን በማጠናከር እና በሩሲያ ግዛት ውስጥ በሚገኙ የኋላ መስመሮች ላይ በተለይም በድሮኖች እና በሚሳኤሎች በመጠቀም አጸፋ እየሰጠች መሆኑ ይገለጻል።
በቅርብ ሳምንታት ውስጥ የድሮን ጥቃቶች መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ሲጨምር፤ ሁለቱም ወገኖች በየዕለቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ድሮኖች በመጠቀም የየራሳቸውን ጥቃት እየሰነዘሩ ይገኛሉ።
ሩሲያ በዩክሬን ከተሞች ላይ በሚሳኤልና በድሮን ጥቃቶችን ያደረሰች ሲሆን፤ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በሚሳኤል ጥቃት የሞቱ እና የቆሰሉ ሰዎች መኖራቸውን መናገራቸው የደረሰውን ጉዳት ያሳያል ተብሏል።
በምዕራባውያን ሀገራት የሚሰጠው የጦር መሳሪያ ድጋፍ እየቀጠለ ሲሆን፤ ዩክሬን አሜሪካ እና ብሪታንያ የሰጧትን ክሩዝ ሚሳኤሎች ወደ ሩሲያ ግዛት መተኮስ መጀመሯ ደግሞ አዲስ ውጥረት ፈጥሯል።
ምዕራባውያን ሀገራት በሩሲያ ላይ የጣሉት ማዕቀብ እና በዩክሬን የሚደረገው ውጊያ የዓለም ኢኮኖሚን እያናጋው ቢሆንም የሰላም ድርድር ጥረቶች ግን እስካሁን ለዘለቄታው ውጤት ሊያመጡ አልቻሉም።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ እርሳቸው ባልተሳተፉበት ውይይት የሚደረስ ማንኛውንም ስምምነት እንደማይቀበሉ መግለጻቸው የሰላም ሂደቱ ምን ያህል ውስብስብ እንደሆነ ያሳያል።
ይህ ግጭት በቅርብ ጊዜ ውስጥ በቀላሉ የመቋጨት ምልክት የማያሳይ ከሆነ፤ አለም አቀፉን ማህበረሰብ በተለይም በአውሮፓ በፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ ደረጃዎች የተወሳሰበ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል ተብሏል።
ሱፊያን አህመድ
ህዳር 25/2018 ዓ.ም
