ባለፈው ሳምንት በቤኒን የተደረገው የከሸፈ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ መሪ ነው የተባለው ግለሰብ በጎረቤት ቶጎ መጠጊያ ማግኘቱን የተለያዩ ምንጮች ዘግበዋል።
የቤኒን መንግስት ባለስልጣናት ለሮይተርስ እንደተናገሩት፤ ሌተናል ኮሎኔል ፓስካል ቲግሪ እና በሙከራው ተሳትፈዋል የተባሉ ሌሎች ግለሰቦች በቶጎ ዋና ከተማ በሚገኘው ‹‹ሎሜ 2›› ሰፈር ተደብቀው ይገኛሉ።
እሁድ ዕለት ቲግሪ ከሰባት ወታደሮች ጋር በቤኒን የመንግስት ቴሌቪዥን ቀርቦ ነበር በወቅቱም ቡድኑ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ታሎንን ከስልጣን ማውረዱን በመግለጽ ቲግሪን እንደ መሪው አስተዋዉቆ ነበር።
ነገር ግን የቤኒን ጦር ኃይሎች፤ በናይጄሪያ ወታደሮች እና በፈረንሳይ የሎጂስቲክስ ድጋፍ ታግዘው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራውን አክሽፈዋል።
አንድ የመንግስት ቃል አቀባይ እንደገለጹት፤ ድርጊቱን ተከትሎ ባሉት ሰዓታት ውስጥ ቢያንስ 14 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ቲግሪ ማምለጥ የቻለ ሲሆን፤ በቀጣይ ቀናትም የት እንደገባ ሳይታወቅ ቆይቶ ነበር።
በቅርቡ በምዕራብ አፍሪካ ከተከሰቱት ተከታታይ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራዎች በኋላ፤ የእሁዱ ክስተት ውጤት ለቀጣናዊ ትብብር ሌላ ፈተና ሆኖ መጥቷል።
የቤኒን ባለስልጣናት፤ቶጎ የሸሹትን ወታደሮች አሳልፋ እንድትሰጥ መጠየቃቸው ተዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ታሎን የከሸፈውን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ‹‹ክህደት››ሲሉ የገለጹት ሲሆን፤ ድርጊቱም ያለ ቅጣት እንደማይታለፍ ተናግረዋል።
እስከዳር ግርማ
ታህሳስ 02/2018 ዓ.ም
