የአፍሪካ ልማት ባንክ አሜሪካ ድጋፏን ብትቀንስም 25 ቢሊየን ዶላር ለማሰባሰብ የለጋሾች ጉባኤ ጀመረ

የአፍሪካ ልማት ባንክ አሜሪካ እያደረገችው ያለውን የድጋፍ መቀነስ ተከትሎ የሚፈጠረውን ክፍተት ለመድፈን ያለመ የለጋሾች ጉባኤ በለንደን አካሂዷል።

ባንኩ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የአፍሪካ ሀገራት በዝቅተኛ ወለድ ብድር ለማቅረብ ያቀደውን የ25 ቢሊየን ዶላር ግብ ለማሳካት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

ይሁንና የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ቀደም ሲል ቃል ገብቶት የነበረውን የ1መቶ97 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ በመከልከሉ፤ባንኩ የያዘው ዕቅድ ላይ ስጋት ፈጥሯል።

በለንደን እየተካሄደ ባለው በዚህ ጉባኤ ላይ አሜሪካ ተወካይ ብትልክም፤የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባት አለመግባቷ ግን እስካሁን በግልጽ አልታወቀም።

የአፍሪካ ልማት ባንክ የሀብት ማሰባሰብ ዘርፍ ኃላፊ ቫለሪ ዳባዲ እንደገለጹት፤ አሜሪካ በዚህ ዙር ተሳትፎ ካላደረገች የ5መቶ60 ሚሊየን ዶላር የገንዘብ ክፍተት ይፈጠራል፡፡
ይህንንም ክፍተት ሌሎች ለጋሽ ሀገራት ብቻቸውን ሊሸፍኑት አይችሉም ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ይህ የሚሰበሰበው ገንዘብ በአፍሪካ ሀገራት ለሚካሄዱ የመስኖ፣ የመንገድ እና የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያነት የሚውል ነው።

የአሜሪካ መንግስት ከዚህ ቀደም ለዓለም ባንክ የልማት ማህበር ይሰጥ የነበረውን ድጋፍ በ8መቶ ሚሊየን ዶላር መቀነሱ የሚታወስ ሲሆን፤አሁን ደግሞ የአፍሪካ ልማት ፈንድን “ወደ መደበኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ተልዕኮው ለመመለስ እንፈልጋለን” ከማለት ውጪ የሰጠው ዝርዝር ማብራሪያ የለም።

ከ1972 ጀምሮ በየሦስት ዓመቱ የሚታደሰው የአፍሪካ ልማት ፈንድ፤እስካሁን ለ37 የአፍሪካ ሀገራት የ45 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን የቲ.አር.ቲ ዘገባዎች ያሳያሉ።

ልዑል ወልዴ

ታህሳስ 07/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *