ኢዜማ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ምርጫን ለማካሄድ መንግስት ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ ጠየቀ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በመጪው ሀገራዊ ምርጫ ወቅት የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ዜጎች የመምረጥ መብታቸውን በነጻነት እንዲጠቀሙ መንግስት ዋስትና ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስቧል።

የፓርቲው አመራር እዮብ ብርሀኑ፤ ሰላምና መረጋጋት ለዲሞክራሲያዊ ምርጫ ቀዳሚው ወይንም “አስቻይ ሁኔታ” መሆኑን ተናግረዋል።

ፓርቲው በሀገሪቱ አንዳንድ ክፍሎች የሚታየው አለመረጋጋት በምርጫው ዝግጅትና አፈጻጸም ላይ ጥላ ሊያጠላ እንደሚችል ስጋቱን ገልጿል።

በተለይም ተፈናቃዮች ያሉባቸው እና ግጭቶች ባልበረዱባቸው ስፍራዎች የምርጫ ጣቢያዎችን መክፈትና የዕጩዎች ምዝገባ ማካሄድ ፈታኝ እንደሚሆን ተመልክቷል።

አመራሩ ከዚህ በተጨማሪም መራጮች ያለምንም ስጋት ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ወጥተው ድምጻቸውን መስጠት የሚችሉበት አስተማማኝ ሰላም ሊሰፍን ይገባል ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎች የጸጥታ ስጋት ሳይኖርባቸው በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ተንቀሳቅሰው የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ እንዲችሉ መንግስት ጥበቃ ሊያደርግላቸው ይገባል ሲልም ነግረዉናል።

የጸጥታ ችግር ባለባቸው መንገዶች ላይ የምርጫ ቁሳቁሶች በሰላም ተንቀሳቅሰው መድረስ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እንዲሰራ ተጠይቋል።

ኢዜማ አያይዞም፤መንግስት የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ያለውን ሁኔታ በዝርዝር በመገምገም፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ልዩ የጸጥታ ጥበቃ ስምሪት እንዲያደርግና የምርጫው ሂደት ፍትሃዊነት እንዳይጓደል ጥረት እንዲያደርግ ጠይቋል።

ለአለም አሰፋ

ታህሳስ 09/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *