የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞቹ የባንክ ሒሳባቸውን ከፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ቁጥር ጋር እንዲያስተሳስሩ፤ካልሆነ ግን ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ በኋላ ምንም ዓይነት የባንክ አገልግሎት ማግኘት እንደማይችሉ አስታዉቋል።
ባንኩ ታኅሣሥ 9 ቀን 2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ ደንበኞች ወደ የትኛውም የንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በመሄድ ባለ 16 አሃዝ የፋይዳ አካውንት ቁጥራቸውን በማቅረብ ከሒሳባቸው ጋር ማገናኘት እንዳለባቸው ገልጾ ይህንን ያላደረጉ ደንበኞች ገንዘብ ማስገባት፣ ማውጣት እና ሌሎች የባንክ አገልግሎቶችን ማግኘት እንደማይችሉ አስጠንቅቋል።
ባንኩ በአዲስ አበባ፣ ሐረሪ እና ድሬዳዋ ደንበኞች እስከ ጥር 1 ቀን 2018 ማስተሳሰር እንደሚችሉ ገልጾ፤ከጥር 2 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ግን ግዴታ እንደሚሆን አስታውቋል።
በትልልቅ የክልል ከተሞችና በወረዳ ዋና ከተሞች ደንበኞች እስከ ጥር 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የጊዜ ገደብ የተሰጣቸው ሲሆን፤ የግዴታ አፈጻጸሙ ከየካቲት 2 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ይተገበራል።
ታህሳስ 10/2018 ዓ.ም
