ኢትዮ ቴሌኮም ላለፉት ስድስት ዓመታት ሲያከናውን የቆየውን ተከታታይ የታሪፍ ቅናሽ እና የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ ተከትሎ አሁን ላይ ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ መጠነኛ የታሪፍ ማስተካከያ ማድረጉን አስታወቀ።
ኩባንያው ማስተካከያውን ያደረገው የሥራ ማስኬጃ ወጪዎች መጨመርን ተከትሎ የአገልግሎቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ መሆኑን ገልጿል።
ኩባንያው ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፣ ባለፉት ስድስት ዓመታት የደንበኞችን የመግዛት አቅም ያገናዘቡ ቅናሾችን በማድረጉ የደንበኞቹን ቁጥር ከ86 ሚሊየን በላይ ማድረስ ችሏል።
በተመሳሳይ የቴሌብር ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ56 ሚሊየን ማለፉን የገለጸው ኩባንያው፤ ይህም ለሀገሪቱ ‘ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025’ ስትራቴጂ ስኬት ትልቅ ሚና መጫወቱን አብራርቷል።
የታሪፍ ማስተካከያው የተደረገባቸውን ምክንያቶች የገለጸው ኢትዮ ቴሌኮም፤ እየታዩ ያሉ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች እንዲሁም የካፒታልና የሥራ ማስኬጃ ወጪዎች መጨመር ዋነኞቹ መሆናቸውን ጠቁሟል።
ይህ እርምጃ ኩባንያው በመላ ሀገሪቱ የጀመረውን የዲጂታል መሠረተ ልማት ማስፋፋት በዘላቂነት ለማጠናከር ያለመ መሆኑም ተገልጿል።
ይሁን እንጂ ማስተካከያው ሲደረግ የማህበረሰቡን የተለያዩ ክፍሎች ተጠቃሚነት ከግምት ውስጥ ያስገቡ ልዩ ድጋፎች መካተታቸውን ኩባንያው አስታውቋል።
ከነዚህም መካከል ደንበኞች በቴሌብር ጥቅል ሲገዙ ያገኙት የነበረው የ10 በመቶ ቅናሽ ወደ 20 በመቶ ከፍ እንዲል መደረጉን ገልጿል፡፡
ታህሳስ 20/2018 ዓ.ም
