የታይላንድ ጦር ከካምቦዲያ ወገን ከ2መቶ50 በላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ሲበሩ መታየታቸውን ገልጿል።
የታይላንድ ጦር ካምቦዲያን አዲስ የተፈረመውን የተኩስ አቁም ስምምነት በመጣስ የከሰሰ ሲሆን፤ ስምምነቱ የተደረሰው ወደ አንድ ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎችን ከመኖሪያ ቀያቸው ባፈናቀለውና ለሳምንታት በዘለቀው ግጭት ማግስት ነበር።
የታይላንድ ጦር ባወጣው መግለጫ፣ እሁድ ምሽት ከካምቦዲያ ወገን ከ2መቶ50 በላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ወደ ታይላንድ ሲበሩ መታየታቸውን ገልጿል።
ሁለቱም ወገኖች የጦር ግንባሮችን አሁን ባሉበት ለማቆም፣ ተጨማሪ ኃይል ላለማሰማራት እና በድንበር አካባቢ የሚኖሩ ሲቪሎች በተቻለ ፍጥነት ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ተስማምተው ነበር።
ይህ ስምምነት በሁለቱ ሀገራት መካከል ለቀናት ከተካሄደው ድርድር በኋላ የተገኘ ትልቅ ውጤት ተደርጎ የታየ ሲሆን፤ በቻይና እና በአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ የተገኘ ነበር።
የታይላንድ ንጉሣዊ ጦር ባወጣው መግለጫ፤የካምቦዲያ ድርጊት ‹‹ትንኮሳ እና ውጥረትን ለመቀነስ የታለሙ እርምጃዎችን መጣስ ነው›› ብሏል።
ድርጊቱ ከተኩስ አቁም ስምምነቱ ውሎች ጋር ‹‹የማይጣጣም›› መሆኑን ገልጿል።
በተጨማሪም ከሐምሌ ወር ጀምሮ በታይላንድ ተይዘው የሚገኙ 18 የካምቦዲያ ወታደሮችን የመልቀቅ ጉዳይን እንደገና መመልከት ሊያስፈልገው እንደሚችል ገልጿል።
የስምምነቶች እና የሀገር ሉዓላዊነት ጥሰቶች የሚቀጥሉ ከሆነ ታይላንድ በዚያው ልክ እርምጃ ለመውሰድ ትገደዳለች ሲል መግለጫው አክሏል።
ካምቦዲያ እስካሁን ስለ ጉዳዩ የሰጠችው አስተያየት የለም።
ይህ ክስ የቀረበው የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በከፍተኛ ጥረት የተገኘውን የተኩስ አቁም ስምምነት ካደነቁ እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፈጣን እና ፍትሃዊ መደምደሚያ በማለት ካወደሱ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ነው።
እስከዳር ግርማ
ታህሳስ 20/2018 ዓ.ም
