የባንግላዲሽ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ኻሊዳ ዚያ በ80 ዓመታቸው ማረፋቸውን ፓርቲያቸው አስታውቋል።
ህልፈታቸው የተሰማው ወደ ስልጣን ይመለሱበታል ተብሎ ከሚጠበቀው ምርጫ ጥቂት ወራት ቀደም ብሎ ነው።
በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄደው ምርጫ አሸንፈው ሀገሪቱን በድጋሚ ይመራሉ ተብሎ ይገመት የነበሩት ኻሊዳ ዚያ፣ ዛሬ ሌሊት ማረፋቸውን የባንግላዲሽ ናሽናሊስት ፓርቲ ገልጿል።
ለዓመታት በጤና እክል እና በእስራት ቢቆዩም፤ ዚያ ባለፈው ህዳር ወር ላይ በየካቲት 2026 ለሚካሄደው ምርጫ ቅስቀሳ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተው ነበር።
ይህ ምርጫ ተቀናቃኛቸው ሼይክ ሃሲና ባለፈው ዓመት በሕዝባዊ አመጽ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ የሚካሄድ የመጀመሪያው ምርጫ ነው።
ከመሞታቸው ጥቂት ሰዓታት በፊት፤ ሰኞ ዕለት የፓርቲው አባላት በስማቸው ለሦስት የምርጫ ክልሎች የዕጩነት ሰነዶችን አስገብተው ነበር።
የእሳቸው ፓርቲ ቢኤንፒም በምርጫው ቀዳሚ ተፎካካሪ ሆኖ ይታያል።
ዚያ በ2018 በሃሲና መንግስት በሙስና ወንጀል ተከሰው የታሰሩ ሲሆን፤ መንግስት ለህክምና ወደ ውጭ ሀገር እንዳይሄዱም አግዷቸው ነበር።
ሃሲና ከስልጣን በተወገዱ ማግስት ባለፈው ዓመት ከእስር ተለቀዋል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በልዩ የአየር አምቡላንስ ወደ ለንደን እንዲሄዱ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ የጤና ሁኔታቸው ግን ለጉዞው የሚያስችል ደረጃ ላይ አልነበረም ሲል ያስታወሰዉ ፍራንስ 24 ነዉ።
እስከዳር ግርማ
ታህሳስ 21/2018 ዓ.ም
